“በ2017 ከ13 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች በሀገራችን ላይ ተሞክረዋል”

7

አዲስ አበባ: መስከረም 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገሪቱ የሚከሰቱ የሳይበር ጥቃቶችን እና ማጭበርበሮችን የመከላከል አቅምን ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ የሳይበር ደህንነት ወር እንደሚከበር የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አሥተዳደር አስታውቋል።

የአሥተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሐሚድ የሳይበር ደህንነት ወር ከጥቅምት 01 እስከ ጥቅት 30/2018 ዓ.ም ድረስ ይከበራል ብለዋል። “የሳይበር ደህንነት ወሩ የዲጂታል ኢትዮጵያ መሠረት” በሚል መሪ መልዕክት እንደሚከበር ነው የገለጹት።

ለሳይበር ጥቃት ምክንያቶች ናቸው ብለው ዳይሬክተሯ ካነሷቸው ነጥቦች ውስጥ የአቅም ማነስ፣ የቴክኖሎጂ ውስብስበነት፣ የሰው ኃይል ችግር እና የግንዛቤ እጥረት ተጠቃሾች ናቸው።

በሀገራችን ሳይበር ዋነኛው የጦር አውድማ በመኾኑ በጂኦፖለቲካል እና ሀገራዊ የውስጥ ጉዳዮች ምክንያት የሳይበር ጥቃት ስጋት እንደኾነም አንስተዋል።

የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበሮች በእጅጉ እየጨመሩ በመኾኑ፤ ከሀገር ወጭም ኾነ ከውስጥ ሊቃጡ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል ወሳኝ መኾኑን መሠረት በማድረግ እና ማኅበረሰባችን እና ተቋማቶቻችን ላይ ጥንቃቄ ስለሚሻ የቀኑ መከበር ወሳኝ ነው ብለዋል።

የዜጎችን እና የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ የሚያሳድጉ መድረኮችን ማዘጋጀት የሳይበር ደህንነት የመከላከል አቅምን ማሳደግ እንደኾነም ገልጸዋል። በወሩ ልዩ ልዩ ሁነቶች በተለያዩ ከተሞች እንደሚዘጋጅ ነው የተናገሩት።

“በ2017 ዓ.ም ከ13 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች በሀገራችን ተሞክረዋል” ነው ያሉት ዳይሬክተሯ።

ስድስተኛው የሳይበር ደህንነት ወር የመከበሩ ግብ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን መሠረት ያደረገ ሀሰተኛ መረጃ መቆጣጠር እና መከላከል የሚያስችል ንቅናቄ ለመፍጠር እንደኾነም ተናግረዋል።

ተቋማትን በድጂታል ደህንነታቸውን የመጠበቅ እና ተጋላጭነታቸውን የመቀነስ ንቅናቄም መፍጠር የወሩ መከበር አንዱ አላማ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ:- አንዱዓለም መናን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአህጉራዊ ነጻ የንግድ ስምምነቱ ትግበራ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል።