አህጉራዊ ነጻ የንግድ ስምምነቱ ትግበራ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል።

3

አዲስ አበባ: መስከረም 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ መሠረት ምርቶቿን ወደ አፍሪካ ሀገራት መላክ ጀምራለች።

ኢትዮጵያ በቀዳሚነት የፈረመችው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት (AfCFTA) ድርድር ተጠናቅቆ የሸቀጦች ዘርፍ የንግድ ትግበራ ተጀምሯል።

በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ በመታገዝም ኢትዮጵያ ምርቶቿን በየብስ እና በአየር ትራንስፖርት ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መላክ ጀምራለች።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የመጀመሪያ ግብይት ማስጀመሪያ መርሐ ግብርም ተካሂዷል። በመርሐ ግብሩ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) አህጉራዊ ነጻ የንግድ ስምምነቱ ትግበራ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል ብለዋል። ለኢትዮጵያ የንግድ ተወዳዳሪነት እና ኢንቨስትመንትን ያነቃቃል፤ ሰፊ የሥራ ዕድልም ይፈጥራል፤ ለሸማቹ ኅብረተሰብም የተሻለ አማራጭ የምርት አቅርቦት ያስገኛል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ፣ በአፍሪካ ሀገራት መካከል የገበያ ትስስርን ለማስፈን የሚያስችል እና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡

አህጉራዊው ነጻ የንግድ ስምምነት የኢትዮጵያን ንግድ ለማዘመን እና ለመላው ዓለም ለመግለጥ የሚያስችል እንደኾነም ተናግረዋል። በእቃዎች ዋጋ ተመን ላይ ስምምነት ተደርሶ፣ የመጀመሪያ የኾነው ጭነት በአየር እና በየብስ መላክ መጀመሩም ተበስሯል።

በተካሄደው ስምምነትም የታሪፍ ምጣኔን ዜሮ አድርጎ በሚደረገው ግብይት የኢትዮጵያን የወጭ ንግድ በትክክለኛው መስመር እና ዕድገት ላይ እየመጣ ያለውን ስኬት ለማሳለጥ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋልም ተብሏል።

የመጀመርያው የንግድ ልውውጥ ትግበራ በምሥራቅ እና በደቡብ አፍሪካ ሀገራት ላይ ትኩረት አድርጓል። በማስጀመሪያ ንግዱም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ ሥጋ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ፣ በየብስ ትራንፖርት ቡና፣ የጥራጥሬ ምርቶች እና የቅባት እህሎች ወደ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኳል፡፡

ይህ ታሪካዊ የንግድ ሥርዓት ትግበራ የበለጠ ውጤታማ እንዲኾን ምርቶችን በጥራት እና በብዛት ማቅረብ የትራንስፖርት እና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትን ማጠናከር ፣ የጉምሩክ ሂደቶችን ማዘመን እና “የጥራት መንደርን” በመጠቀም የምርቶችን ጥራት ማረጋገጥ አስፈላጊ መኾኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፦ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መልካም” የማሽላ ምርጥ ዘር አርሶ አደሮችን ውጤታማ እያደረገ ነው።
Next article“በ2017 ከ13 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች በሀገራችን ላይ ተሞክረዋል”