
ከሚሴ: መስከረም 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተሻሻለ የማሽላ ምርጥ ዘር በመጠቀማቸው ምርት እና ምርታማነታቸው እየጨመረ መምጣቱን በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የደዋ ጨፋ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
እንደ ሀገር በግብርናው ዘርፍ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን ለማቅረብ እና ግብርናውን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየተሠራ ነው።
በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የደዋ ጨፋ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የአርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ እና የተሻሻለ የምርጥ ዘር አቅርቦትን ችግር ለመቅረፍ የዘር ብዜት ላይ እየሠራ ይገኛል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የደዋ ጨፋ ወረዳ ሸክላ ቀበሌ አርሶ አደሮች የተሻሻለ የማሽላ ምርጥ ዘር በመጠቀማቸው ምርት እና ምርታማነታቸው እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
“መልካም” የተሰኘ የተሻሻለ የማሽላ ምርጥ ዘር በመጠቀማቸው በአጭር ጊዜ የተሻለ ማምረት እንዳስቻላቸው ነው የገለጹት።
ከዚህ ቀደም ከሄክታር 20 ኩንታል ምርት ይሰበስቡ እንደነበር ገልጸዋል። አሁን ላይ የተሻሻለ ምርጥ ዘር በመጠቀማቸው በሄክታር ከ40 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
የሸክላ ቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በቀበሌው ከ68 ሄክታር መሬት በላይ በመልካም ማሽላ ዘር ብዜት መሸፈኑን ገልጸዋል። የአርሶ አደሮች የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን የመጠቀም ልምዱ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።
የደዋ ጨፋ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንድሪስ መሐመድ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የተሻሻሉ የማሽላ ምርጥ ዘርን ለማቅረብ በተሠራው ተግባር በወረዳው ከ140 ሄክታር መሬት በላይ በመልካም ማሽላ ዘር መሸፈን መቻላቸውን አስረድተዋል።
በወረዳው ከ5 ሺህ 600 ኩንታል በላይ ምርት በመሰብሰብ በዩኒዬኖች በኩል በአጎራባች ዞኖች እና በክልሉ ያለውን የተሻሻለ የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!