“ጠንካራ የዳኝነት ሥርዓት እንዲኖር የክልሉ መንግሥት ጽኑ ፍላጎት አለው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

10

ባሕር ዳር: መስከረም 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከመስከረም 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ “የጋራ ራዕይ ለጠንካራ የዳኝነት ሥርዓት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች ጉባኤ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎችም የክልል እና የፌዴራል መንግሥት መሪዎች ተገኝተዋል።

በጉባኤው ተገኝተው የማጠቃለያ መልዕክት እና የሥራ መመሪያ ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ “ጠንካራ የኾነ የዳኝነት ሥርዓት እንዲኖር የክልሉ መንግሥት ጽኑ ፍላጎት አለው”፤ በትኩረትም እየተሠራ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች እና ዲጂታል የችሎት አሠራርን ለመዘርጋት እየተደረገ ያለውን ጥረት የክልሉ መንግሥት እየተከታተለ እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል።

በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመረው ዘመናዊ እና ምቹ የሥራ ቦታ ግንባታ ወደ ዞን እና ወረዳዎች ማደግ እንደሚገባውም ርእሰ መሥተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የዞን እና የወረዳ ዳኞች እና የፍርድ ቤት የሥራ ኀላፊዎች በየደረጃው ከሚገኙ ሥራ አሥፈጻሚዎች ጋር በቅርበት በመወያየት እና ከሕዝቡ ጋር በመነጋገር ለለውጥ መሥራት፣ አስፈላጊ ግብዓቶችንም ማሟላት፣ ነጻ እና ገለልተኛ የኾነ የፍትሕ ሥርዓት መገንባት አለባቸው ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ።

የዳኝነት ሥርዓቱ ከየትኛውም አካል ጣልቃ ገብነት የጸዳ ኾኖ ሕዝቡን የሚያረካ፣ መልካም አሥተዳደርን የሚያሰፍን እና ለልማት ምቹ መደላድል የሚፈጥር መኾን እንደሚገባውም ገልጸዋል።

ነጻ እና ገለልተኛ ኾነው ሕዝብን የሚያገለግሉ በርካታ ዳኞች እንዳሉ ሁሉ የሥነ ምግባር ጉድለት የሚስተዋልባቸው ዳኞችም ስለማይጠፉ ተከታትሎ ማረም እና ማስተካከል ይገባል ብለዋል።

ዳኞች በሥነ ምግባር፣ በዕውቀት እና በክህሎት የታነጹ እንዲኾኑ የሚያስችሉ ሥልጠናዎች መመቻቸት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ጉባኤው ዳኞች የሀገርን እድገት፣ መልካም አሥተዳደርን እና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ነው ብለዋል። ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር እና በማስከበር ረገድ ዳኞች ያላቸውን ሚና በውል እንዲረዱ የዳኝነት እና የመሪነት ሚናቸውንም እንዲወጡ ለማስቻል የተዘጋጀ ጉባኤ ስለመኾኑም አንስተዋል።

ዳኞች ከንግድ እና ልማት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ክርክሮችን በአፋጣኝ እልባት በመስጠት፣ ወንጀል ስለመፈጻማቸው በማስረጃ የተረጋገጠባቸውን አካላት በመቅጣት የሕግ የበላይነትን ማስፈን ይገባቸዋልም ብለዋል።

ዳኞች ከሕግ የሚያፈነግጠውን የማኅበረሰብ ፀባይ ለማረቅ ከፍተኛ ኀላፊነት የተሰጣቸው የማኅበረሰብ መሪዎች ናቸው ነው ያሉት፡፡

በዚህ ጉባኤ ላይ በስፋት ውይይት ከተደረገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል የክልሉ ፍርድ ቤቶች የሙያ ሥነ ምግባር ግንባታ እና የሙስና መከላከያ ስትራቴጅ አንዱ ነው ብለዋል።

አዲሱን የሙያ ሥነ ምግባር ደንብ ሳይሸራረፍ ለማስከበር ይሠራልም ብለዋል። በዳኞች ሥነ ምግባር ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እና ተጠያቂነትን ማስፈን የዚህ በጀት ዓመት ዋነኛ ተግባር ነው፤ ለዚህም ሁሉም ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች እንዲሁም የፍርድ ቤት መሪዎች የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ትግበራ ላይ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። ተጨባጭ እና ተምሳሌት ሊኾኑ የሚችሉ ውጤቶች ስለመመዝገባቸውም ተናግረዋል።
እነዚህ ለውጦች እንዲመዘገቡ የክልሉ መንግሥት ልዩ ክትትል እና ድጋፍ ስለማድረጉም ተናግረዋል።

የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ከዳር ለማድረስ ከፍተኛ የኾነ የመሪ ቁርጠኝነት እና ቁጭት እንዲሁም የአጠቃላይ ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ከፍተኛ መነሳሳት
ተፈጥሯልም ብለዋል።

በሥራዎች ላይ የሚገጥሙ ተግዳሮቾችን ለመፍታት ደግሞ የክልሉ መንግሥት እና በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሁለት ዓመታት ከትምህርት መራቅ ለሥነ ልቦና ጉዳት ዳርጎን ቆይቷል።
Next article“መልካም” የማሽላ ምርጥ ዘር አርሶ አደሮችን ውጤታማ እያደረገ ነው።