
ደብረ ማርቆስ: መስከረም 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የትምህርት ዘርፉ ጉዳት አጋጥሞት ቆይቷል። የጸጥታ ችግሩ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲኾኑ ምክንያት ኾኗል።
በጸጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት ተቋርጦባቸው ከቆዩ አካባቢዎች ደግሞ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የእናርጅ እናውጋ ወረዳ አንደኛው ነው። ወረዳው አሁን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።
የእናርጅ እናውጋ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ተሾመ ኀይሉ የልጆች የነገ ራዕይ እንዳይጨልም እና ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመገንባት ትምህርት ወሳኝ ተግባር ነው ብለዋል። ከየትኛውም የፖለቲካ ፍላጎት ነጻ በኾነ መንገድ እንዲሰጥ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ወላጆች እና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለትምህርት ዘርፉ የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት የመጠገን ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
ተማሪዎችም ለሁለት ዓመታት ከትምህርታቸው ርቀው በመቆየታቸው የሥነ ልቦና ጉዳት እንደገጠማቸው ተናግረዋል። አሁን ላይ ወደ ትምህርት በመመለሳቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የተማሪ ወላጆችም የልጆቻቸው ሕይወት እንዲለወጥ እና ከዘመኑ ጋር እንዲራመዱ የትምህርት መጀመር እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
በወረዳው ከ70 በላይ የትምህርት ተቋማት አሉ። ከአስር በላይ ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራ ገብተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!