
ባሕር ዳር: መስከረም 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በሥነ ምግባር ግንባታ እና ሙስናን በመከላከል ዙሪያ ከክልል የመንግሥት ተቋማት እና የልማት ድርጅቶች ኦዲተሮች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ወቅታዊ የሥነ ምግባር እና የሙስና ችግር ያለበት ደረጃ፣ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት እንዲኹም ከባለድርሻ አካላት ስለሚጠበቀው አበርክቶ የውይይት ሀሳብ ቀርቧል።
ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየት የውስጥ ኦዲተሮች የተሰጣቸውን ኀላፊነት በመፈጸም በኩል እንደየተቋማቱ የሚለያይ መኾኑን ገልጸዋል። ኦዲተሮች ላይም ውስንነት መኖሩ ተጠቅሷል።
በኦዲት ግኝቶች ላይ ፈጥኖ እርምጃ የመውሰድ እና የማስመለስ ውስንነት መኖሩ፣ ለግኝት ትኩረት በመስጠት በኩል የመሪ ወጥ አቋም አለመኖርም መስተካከል እንዳለበት ተነስቷል።
የአቅም ግንባታ ሥራን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ፣ ብልሹ አሠራርን እና ሙስናን በመከላከል በኩል ተቋማት የሚለኩበት መስፈርት እና ውድድር እንዲኖር፣ የኦዲት ግኝት በተቀናጀ መልኩ እየተገመገመ እንዲመራም አስተያየት ተሰጥቷል።
ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሙስና የሚፈጸምበትን የረቀቀ ስልት እና ለሙስና የበለጠ ተጋላጭ የኾኑ ተቋማትን ለይቶ አሠራሮችን ማስተካከል እንደሚጠበቅበት ተነስቷል።
የግዢ፣ የንግድ እና የመሬት አሥተዳደር ሥርዓቶች ለሙስና የተመቹ እና ከተለመደው የአሠራር ሥርዓት ባለመውጣታቸው ማስተካከያ መደረግ እንዳለበት ተነስቷል።
ትላልቅ የሙስና ግኝቶችንም ለሕዝብ ማጋለጥ እንደሚገባ ነው የተመከረው።
የኦዲተሮች በቴክኖሎጂ የመብቃት እና ተጠሪነታቸውም ለገንዘብ ቢሮ መኾን አቅም እና ነጻነት ይኖረዋል ተብሏል።
የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሚስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ በውይይቱ የተነሱ ሀሳቦችን ይዘው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ብልሹ አሠራርን እና ሙስናን ለመከላከል የመንግሥትን ቁርኝነት ገልጸው ለዚህም የበቃ ተቋም ለመገንባት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
አሠራሮችን ዲጂታላይዝድ ማድረግ አንዱ የሙስና መከላከል ስልት መደረጉን አንስተዋል። መሬትን በካዳስተር ሥርዓት በማሥተዳደርም ችግሩን ለማቃለል እንደሚሠራም ጠቅሰዋል።
ችግሩ ውስብስብ ስለኾነ መተጋገዝን እንደሚጠይቅ እና ኦዲተሮች ግኝቶችን ለሥነ ምግባር መከታተያ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አማረ ብርሃኑ (ዶ.ር) ኦዲተሮች ነጻና ገለልተኛ ኾነው የመሥራታቸውን መርሕ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዘርፉ ውጤታማ ኾኖ ብልሹ አሠራርን ለመከላከል የሙያ ብቃትን የማሳደግ አስፈላጊነት አንስተዋል። የአሠራር ስልትን በማበጀት መከላከል ላይ ላተኮረ ሥራ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
ለሥራዎች ውጤታማነት የተግባቦትን አስፈላጊነት ጠቅሰው ግልጽ ሪፖርት ማቅረብ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በአሠራር ላይ ያሉ 39 የሕግ ክፍተቶችን እንዲሻሻሉ ለሚመለከተው አካል ማቅረቡን አንስተዋል።
በቀጣይ የኦዲት ሪፖርቶች ለሕዝብ ተደራሽ በሚኾን መልኩ እናቀርባለን ብለዋል።
መንግሥት በቅንጅት በመሥራት ሙስናን የመከላከል ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ነው ዋና ኦዲተር አማረ ብርሃኑ የተናገሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!