
ደባርቅ: መስከረም 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አረጋውያንን በዘላቂነት ለመደገፍ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናዎነ እንደሚገኝ የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ገልጿል።
በመቄዶንያ የአረጋውያን፣ የአቅመ ደካሞች እና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ደባርቅ ቅርንጫፍ ከሚገኙት አረጋውያን መካከል ፲ ዓለቃ ብርሃኑ ማሙየ ይገኙበታል።
ውድ የሕይዎት መስዋዕትነት በሚያስከፍለው የውትድርና ሙያ ዘርፍ ተሰማርተው ሀገራቸውን ማገልገላቸውን ያነሳሉ።
በግዳጅ ወቅት በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት በሕክምና ሲረዱ መቆየታቸውን እና በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ በተሟላ እንክብካቤ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
አረጋውያን በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ሀገር እና ወገንን ያገለገሉ ባለውለታዎች በመኾናቸው መደገፍ እና መንከባከብ እንደሚገባም አብራርተዋል።
ሌላው በማዕከሉ አሚኮ ያገኛቸው አባ ጌታነህ ተገኘ በግብርና ዘርፍ ተሰማርተው ሀገር እና ወገንን ሲጠቅሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በደረሰባቸው የጤና እክል ምክንያት ለችግር በመጋለጣቸው ወደ ማዕከሉ መጥተው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መኾናቸውን ነው የነገሩን።
አረጋውያንን እና አቅመ ደካሞችን መደገፍ እና መርዳት በሃይማኖት አስተምህሮም ኾነ በሥነ-ምግባር ሕግ የሚደገፍ ተግባር ነው ብለዋል።
በመቄዶንያ የአረጋውያን፣ የአቅመ ደካሞች እና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ደባርቅ ቅርንጫፍ አሥተባባሪ ሰላም አምባቸው ማዕከሉ በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች አቅመ ደካሞችን እና የአዕምሮ ሕሙማንን እያገዘ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አረጋውያንን እና አቅመ ደካሞችን መደገፍ የሁሉም ማኅበረሰብ ክፍል ኀላፊነት ሊኾን እንደሚገባም አስረድተዋል።
አረጋውያን እናቶች እና አባቶችን መደገፍ የዚህ ትውልድ ሀገራዊ ግዴታ መኾኑንም ነው የጠቆሙት።
የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ባንች አምላክ መልካሙ አረጋውያንን በዘላቂነት ለመደገፍ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናዎኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
አረጋውያንን ከመደገፍ ባለፈ አቅማቸውን ባገናዘበ የሥራ መስክ ተሰማርተው ራሳቸውን መደገፍ የሚችሉበትን ኹኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የአቅመ ደካማ እና የአረጋውያን መርጃ ማዕከላትን የማጠናከር እና ተደራሽነታቸውን የማስፋት ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!