በሩብ ዓመቱ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሠቡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

9

ባሕርዳር: መስከረም 29/2018ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሦሥት ወራት ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሠቡ ተገልጿል።

ወይዘሮ አበቡ ሞላ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ ናቸው። ግብር መክፈል ሀገራዊ ግዴታ ነው ብለዋል።

“ግብር በመክፈል እንደ ዜጋ ሀገራዊ ግዴታየን እየተወጣሁ ነው” ያሉት ወሮ አበቡ የሚጣልባቸው ግብር ከማኅበረሰቡ የሚሠበሠብ እና በሥራው ከተገኘው ትርፍ ላይ የሚጣል በመኾኑ የሂሳብ መዝገብ መያዝ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። ካሽ ሪጂስተር ማሽንን በሚገባ በመጠቀም ግብርን ያለ ችግር እንደሚከፍሉም ገልጸዋል።

የደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ ግብሩ ከፈተኛ በመኾኑ እንደየ አስፈላጊነቱ በሁለትም ኾነ በሦሥት ወራት ግብራቸውን እንደሚከፍሉ አንስተዋል።

የመረጃ አያያዛቸው ኮምፒተራይዝድ እንደኾነ የጠቆሙት ግብር ከፋዩዋ ድርጅታቸው የሒሳብ ባለሞያ እንዳለውም ተናግረዋል።

የሒሳብ ባለሙያው የቀን ውሎውን ሒሳብ ከሠራ በኋላ ገቢ እና ወጭ እንደሚያሳውቅም አስረድተዋል። በተሠራው ሂሳብ መሠረትም ለመንግሥት ገቢ የሚኾነውን ገንዘብ ገቢ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።

ግብር ለመክፈል ሰላም አስፈላጊ ነው ያሉት ወይዘሮ አበቡ ሰዎች ሰላም ተሰምቷቸው ወጥተው ሲገቡ፤ ሲገበያዩ፣ ነጋዴውም መንግሥት የሰጠውን ግብር የመሠብሠብ ኀላፊነት በአግባቡ መወጣት እንደሚችል ነው የገለጹት።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ታዘባቸው ጣሴ ቢሮው የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የሚታቀዱ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ አቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት ከመደበኛ እና ከከተማ አገልግሎት ገቢ 100 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ አቅዶ እስከ መስከረም 27/2018 ዓ.ም በተሠበሠበ ዕለታዊ መረጃ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ መሠብሠብ ተችሏል ብለዋል።

የገቢ አሠባሠቡን ለማሳድግ እና ለማሳለጥ፣ ከንክኪ ነጻ ለማድረግ የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች የሒሳብ መዝግብ በመያዝ ግብራቸውን ያሳውቃሉ ብለዋል።

የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ደግሞ ዓመታዊ ግብራቸውን ከሐምሌ 1 እስከ ጳጉሜ 5 ያሳውቃሉ። በገቢ ማሳወቂያ ወይም የሒሳብ መዝገብ እንዲይዙ በመደረጉ ውጤት ታይቶበታል ብለዋል።

ቢሮው የታክስ አሥተዳደር ሥርዓቱን ለማዘመን በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደኾነም አስገንዝበዋል። ከዚህም ውስጥ አንዱ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፈዮች ግብራቸውን በቤታቸው ወይም በድርጅታቸው ሥራ ላይ ኾነው የሚከፍሉበትን ኢ-ታስ የተሰኘ ዘመናዊ አሠራር በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አስለምቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

ቅንጅታዊ አሠራርን ማጎልበት፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራርን መዘርጋት ለገቢ አሠባሠቡ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

የደረጃ “ሀ” እና የደረጃ “ለ”ግብር ከፋዮች መዝገብ ይዘው እንዲሠሩ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።

በክልሉ 22 ሺህ 930 የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች አሉ ያሉት ዳይሬክተሩ በዚህ ሦሥት ወር ከተሠበሠበው ገቢ ግብራቸውን አሳውቀው የከፈሉ 4 ሺህ 4 እንደኾኑም ጠቁመዋል።

በርካታ ግብር ከፋዮች አሁንም ግብራቸውን አሳውቀው እንዳልከፈሉ ገልጸዋል። በቀሪ ጊዜያት ግብራቸውን አሳውቀው እንዲከፍሉም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ሰመሀል ፍስሀ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዘመቻ የሚሰጠው የፖሊዮ ክትባት ውጤታማ እንዲኾን ሁሉም መረባረብ አለበት።
Next articleአረጋውያንን ከመደገፍ ባለፈ አቅማቸውን ባገናዘበ የሥራ መስክ ለማሰማራት ጥረት እየተደረገ ነው።