በዘመቻ የሚሰጠው የፖሊዮ ክትባት ውጤታማ እንዲኾን ሁሉም መረባረብ አለበት።

9

ባሕር ዳር: መስከረም 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኅብረተሰቡ ከ10 ዓመት በታች የኾኑ ሕጻናትን የፖሊዮ ክትባት እንዲያስከትብ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥሪ አቅርቧል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም ድረስ የሚሰጠውን የፖሊዮ ክትባት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ክትባቱ መደበኛ ክትባት ሳይኾን በደቡብ ጎንደር ዞን አንዳቤት ወረዳ እና ጎንደር ከተማ አሥተዳደር የልጅነት ልምሻ በሽታ በመገኘቱ ለወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

ክትባቱ በሽታው በተገኘባቸው እና አጎራባች በኾኑ አካባቢዎች እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡ ጎንደር ከተማ ፣ ደብረ ታቦር ከተማ፣ ባሕር ዳር ከተማ እና ደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደሮች፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ጎጃም እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ክትባቱ የሚሰጥባቸው ናቸው ተብሏል። ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ሕጻናት ክትባቱን ለመስጠት በዕቅድ መያዙንም አስታውቀዋል፡፡ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የኾኑ ሁሉም ሕጻናት ክትባቱን እንደሚወስዱም ተናግረዋል፡፡

ክትባቱ በቤት ለቤት፣ በትምህርት ቤቶች እና በመጠለያ ጣቢያዎች በአፍ በጠብታ መልክ የሚሰጥ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር ፖሊዮን ማጥፋት አለብን ያሉት ዳይሬክተሩ በሽታው እጅ እና እግርን በማስለል ዘላቂ የአካል ጉዳት የሚያስከትል በቫይረስ የሚተላለፍ አደገኛ በሽታ ነውም ብለዋል፡፡

ይህንን አደገኛ በሽታ በክትባት መከላከል ይቻላል ነው ያሉት፡፡ ፖሊዮን ለማጥፋት መደበኛ ክትባቱን ከ90 በመቶ በላይ ማድረስ እና የበሽታ ቅኝት ሥራዎችን ማጠናከር አስፈላጊ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ይህ ክትባት ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም ድረስ በአራት ቀናት ማለቅ አለበት ነው ያሉት፡፡ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት የተዘለሉ እና በችግር ምክንያት ክትባት ያልወሰዱ ካሉ በማጣሪያ ሁለት ቀናት ክትባቱ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡

ለዚህ ክትባት ከ8 ሺህ 835 በላይ የክትባት ቡድን እና ከ3 ሺህ 224 በላይ የክትባት አስተባባሪዎች ይሠማራሉ ብለዋል፡፡ ከ26 ሺህ በላይ ክትባቱን የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች ይሳተፋሉ ነው ያሉት። አስፈላጊው የክትባት ቁሳቁስ አቅርቦት ቅድመ ዝግጀት ተደርጓልም ብለዋል፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ቤት ለቤት ሲንቀሳቀሱ ሁሉም አካል ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራን፣ የአሥተዳደር አካላት፣ ሚዲያዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አንድም ሕጻን ሳይከተብ እንዳይቀር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

አንድም ሕጻን ሳይከተብ ከቀረ እና በሽታው ከተከሰተ ድጋሚ ወደ ዘመቻ እንገባለን፤ ክትባት ማግኘት የሕጻናት መብት በመኾኑ እንዲከተቡ ሁሉም አካል መተባበር አለበት ነው ያሉት፡፡

ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የኾኑ ክትባት ያቋረጡ እና ለአንድ ዓመት መደበኛ ክትባት ያልወሰዱ ሕጻናት ደግሞ በጤና ተቋማት በሁሉም የክልሉ ክፍሎች እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ ቤተሰብ ልጆቻቸውን ወደ ጤና ተቋማት እና ጊዜያዊ የክትባት ጣቢያዎች በመውሰድ ማስከተብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በክትባት ዘመቻው ላይ አላስፈላጊ መረጃዎችን በመተው ኅብረተሰቡ ከኢንስቲትዩቱ የሚወጡ መረጃዎችን ብቻ በመከታተል እንዲተገብር አሳስበዋል።

የክትባት ቁሳቁስ በተለያዩ የመጓጓዣ አይነቶች የሚደርስ በመኾኑ ሁሉም አካል እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡ ይህንን ዘመቻ ማስተጓጎል ሕጻናት ክትባት እንዳያገኙ ማድረግ ነውም ብለዋል፡፡ ሰብዓዊነት ለኾነው ተግባር ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጋራ ዲጂታል ነጋችንን ለማሳደግ በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleበሩብ ዓመቱ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሠቡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።