
ባሕር ዳር: መስከረም 29/2018ዓ.ም (አሚኮ) ግብጽ ከትናንት እስከ ዛሬ የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ፣ አንድነቷን ለመከፋፈል እና መንግሥታዊ ሥርዓቷን ለማፍረስ የጥፋት እጆቿ ረጅም ናቸው።
ዳምጠው ተሰማ (ዶ.ር) በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት መምህር ናቸው። የግብጽ ዋነኛ ዓላማ ኢትዮጵያን በመከፋፈል እና በየቦታው የኮሰመኑ አሻንጉሊት መንግሥታትን በመመሥረት የዓባይን ወንዝ ከምንጩ መቆጣጠር ነው። ለዚህ ደግሞ ከትናንት እስከ ዛሬ ሴራዋን በተራቀቀ መንገድ ቀጥላለች ይላሉ ምሁሩ።
ግብጽ የኢትዮጵያን መዳከም የፖለቲካ እና የውጭ ፖሊሲ ታክቲኳ አድርጋ አሁንም መቀጠሏን ምሁሩ አብራርተዋል፡፡ የግብጽ ሴራ የቅርብ ጊዜ አይደለም የሚሉት ዶክተር ዳምጠው ኢትዮጵያ ሰላም ውላ ሰላም እንዳታድር በፍጹም አትፈልግም ነው ያሉት፡፡
ቀደም ባለው ዘመን ኢትዮጵያ እንድትከፋፈል በመሻቷም የሻዕቢያ ቢሮ በግብጽ መዲና ካይሮ ከተማ መከፈቱን አስታውሰዋል፡፡
”ኢትዮጵያን እገነጥላለሁ አስገነጥላለሁ” የሚል አጀንዳ ያለው ኀይል ሁሉ የሚሠባሠበው በግብጽ መኾኑ ሀገሪቱ ምን ያህል ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሠራች እንደኾነ ያሳያል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያን በማዳከም እዚህም እዚያም ”ሀገር እንኾናለን” ለሚሉ ሀገር በቀል ከሃዲዎች እና የኢትዮጵያን መሬት ለመቁረስ ላኮበኮቡት የውጭ ወራሪዎች ግብጽ መጠነ ሰፊ እርዳታ እየሰጠች መኾኗንም ዶክተር ዳምጠው ተናግረዋል።
ከሰላማዊ እንቅስቃሴ ውጭ በኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ላይ አምጻለሁ ለሚል ሁሉ ግብጽ ዕቅድ አውጥታ በመስጠት፣ የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ እና ዘርፈ ብዙ የሎጀስቲክ ድጋፍ ስታደርግ ኖራለች ነው ያሉት።
የቅርቡን ጊዜ የግብጽን ሴራ ብንመለከት ኢትዮጵያ የባሕር በር ችግሯን በምሥራቅ በኩል ለመፍታት ከሶማሊያ ላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ላይ ስትደርስ መጀመሪያውን የጥላቻ ቀይ ካርድ የመዘዘችው እና የተቃውሞ ሀሳቧን በዓለም አቀፍ የመገናኛ አውታሮች ያሰማችው ይህችው ሀገር ናት፡፡ ኤርትራንም ከኋላዋ እንድትከተል አድርጋለች ብለዋል፡፡
የሶማሌ ላንድ ሕዝብም በኢትዮጵያ ላይ ተቃውሞ እንዲያሰሙ ለማነሳሳትም ያላደረገችው ነገር የለም፡፡ ለሀገሪቱ ከአሁን በፊት አድርጋው የማታውቀውን ድጋፍ ለማድረግም እንዳኮበኮበች ነው ምሁሩ የተናገሩት፡፡
ግብጽ ከሰሜን አፍሪካ ተንደርድራ በመምጣት ምሥራቅ አፍሪካዊቷን ሶማሊያን እና ሶማሌ ላንድን መሸጋገሪያ ድልድይ በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዳይከበር እያሴረች እንደምትገኝ ነው ምሁሩ ያብራሩት፡፡
በየትኛውም በኩል ኢትዮጵያ ወደ የትኛውም ባሕር እንዳትጠጋ ለማድረግ ኢትዮጵያን ማዳከም የግብጽ ፍላጎት እና ዓላማ መኾኑን ምሁሩ ተናግረዋል፡፡
ግብጽ ሱዳንን በማስከተልም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማኮላሸት ከትናንት ጀምሮ እያሴረች ነው ብለዋል፡፡
በቅርቡ ሕወሓት ከሕዝብ ተነጥሎ በየኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሲከፍት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እና መጠለያ ይሰጠው የነበረው ከሱዳን እንደነበር አንስተዋል።
ቀደም ብሎ በነበረው ጊዜም ሻዕቢያ እና ሕወሓት ቅንጅት ፈጥረው ኢትዮጵያን ሲያደሙ ታንክ አሰልፋ የተዋጋችው ሱዳን መኾኗ ሀገራቱ ኢትዮጵያን ለማዳከም እና ለመከፋፈል የሚያሴሩትን ሴራ ፍንትው አድርጎ ያመላክታል ነው ያሉት፡፡
የዓባይ ወንዝን በተመለከተ በቅኝ ግዛት ዘመን የተደረሰው ውል ኢትዮጵያን ያገለለ ነበር ያሉት ዶክተር ዳምጠው ይህን የተሳሳተ እና የተንሸዋረረ ውል ማስቀጠል የግብጽ ፍላጎት መኾኑንም ምሁሩ አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን በፍትሐዊነት ተጠቅመን እናልማ በማለቷም ግብጽ ቋሚ ጠላት አድርጋታለች ነው ያሉት፡፡
”ኢትዮጵያ አንድነቷን አጠናክራ መብቷን ማስከበር ከጀመረች የውኃ ሃብቷን ለልማት ታውላለች፤ ይህ ደግሞ ለግብጽ ችግር ይፈጥራል በሚል የተሳሳተ እሳቤ እየተንቀሳቀሰች ያለችው ሀገሪቱ ኢትዮጵያን በማዳከም የዓባይን ወንዝ መቆጣጠር ይገባል” በሚል ቀቢጸ ተስፋ እየሠራች ነው ብለዋል፡፡
አብረዋት በቅንጅት የሚያሴሩ ታሪካዊ ጠላቶችን አደብ ለማስገዛት ኢትዮጵያ የበለጠ ራሷን ማልማት አለባት ነው ያሉት፡፡ የመደራደር አቅሟንም ማሳደግ እንዳለባት ነው ምሁሩ የጠቆሙት፡፡
የትኛውም ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን ጥቅም እቆማለሁ የሚል የፖለቲካ ድርጅት፣ ፖለቲከኛ ወይም ሃይማኖተኛ በምንም መንገድ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር መሰለፍ የለበትም ነው ያሉት ምሁሩ፡፡
ልዩነት ያለውም ኾነ በሥራ ሂደት የተከፋ ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር መሥራት ግን ከነውርም በላይ ሀገርን መሸጥ ነው ብለዋል፡፡
ግብጽ ከቅርብም ከሩቅም የእርሷን የተሳሳተ እሳቤ የሚከተሉ ሀገራትን ወይም የኢትዮጵያን ሕዳሴ የማይሹ የሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎችን በማስተባበር እና በትጥቅ በመደገፍ የኮሰመነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በእንቅልፍ አልባነት እያሴረች መኾኗን ምሁሩ አስረድተዋል፡፡
የዓባይን ወንዝ ጠቅልሎ መያዝ ብቻ ሳይኾን የግብጽ ሴራ ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር የማራቅም ነው፡፡ “ቀይ ባህርን የአረብ ሀገራት ባህር ብቻ እናደርገዋለን “በሚል ዕቅድ የሰከረችው ግብጽ ስትራቴጂክ ዓላማዋ ኢትዮጵያን ማዳከም እና የዓባይ ወንዝን ከምንጩ ለመቆጣጠር እንደኾነ ነው ያብራሩት፡፡
የግብጽ መሪዎች “የዓባይን የውኃ ፍሰት የሚነካ ወይም የሚያዳክም ማንኛውንም ርምጃ ካስፈለገ በጦር ኀይልም ቢኾን እንቀለብሳለን” በማለት ጣቷን ወደ ኢትዮጵያ መቀሰሯን ያየ ኢትዮጵያዊ ግብጽን በዓይነ ቁራኛ መመልከት እንዳለበት ነጋሪ ነው ብለዋል፡፡
የአሁኖቹ የግብጽ መሪዎችም የዓባይ ወንዝን ከምንጩ ለመቆጣጠር ኢትዮጵያን ማተረማመስ እና መበታተን በፖሊሲ ደረጃ ነድፈው እየሠሩበት እንደኾነም ነው ምሁሩ የተነተኑት፡፡
የኢትዮጵያ የመገናኛ አውታሮች ያለልዩነት፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና አንቂዎች ግብጽ ለምን ኢትዮጵያ እንድትኮሰምን ትፈልጋለች የሚለውን ሃሳብ በጥንቃቄ እየመረመሩ ለሕዝብ ማስረጽ እንደሚገባም ነው ዶክተር ዳምጠው ተሰማ የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!