
ባሕር ዳር: መስከረም 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በሥነ ምግባር ግንባታ እና ሙስናን በመከላከል ዙሪያ ከክልል የመንግሥት ተቋማት እና የልማት ድርጅቶች ኦዲተሮች ጋር እየመከረ ነው።
የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ ተቋማቸው በተቋማት የሚታዩ ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል ጥናት በማድረግ ክፍተቶችን ለማረም እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ብልሹ አሠራሮችን በመከላከል በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የተቋም ኀላፊዎች ተቀናጅተው ለመሥራት በጋራ አቅደው ወደ ሥራ መግባታቸውንም አንስተዋል።
ሙስናን ቀድሞ ለመከላከል የውስጥ ኦዲተሮች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የገለጹት ኮሚሽነር ሀብታሙ ውይይቱም ይህንኑ ለማጠናከር የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል። የሕዝብ እና የመንግሥት ሀብት እንዳይመዘበር ለመከላከል ጉልህ ድርሻ ካላቸው ሌሎች አካላት ጋርም መሰል ውይይት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በመድረኩ የውስጥ ኦዲተሮች አሠራርን ጠብቀው ምዝበራን ለመከላከል ሲሠሩ ያሉ ክፍተቶች ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል። ከዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባለሙያዎች ጋርም በመወያየት ችግሮችን የመፍታት፣ አቅም እና መነሳሳት የመገንባት ሥራ እንሠራለን ብለዋል።
በሀገር ደረጃ የሚመደበው በጀት ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰዋል። ነገር ግን የመንግሥትን የፋይናንስ ሥርዓት ጠብቆ የመጠቀም ችግር መኖሩን ገልጸዋል። ችግሮቹንም የውስጥ ኦዲተሮች ስለሚያውቋቸው በመፍትሔያቸው ላይ ውይይት በማድረግ ለቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይገባል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!