
ባሕርዳር: መስከረም 29/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማኅበር በአማራ ክልል ለአነስተኛ እና መካከለኛ የንግድ አንቀሳቃሾች የብድር አቅርቦት ተግዳሮቶች፣ የገበያ ማረጋጋት፣ የሥራ ፈጠራ ፖሊሲ እና አዋጅን በተመለከተ ከመንግሥት፣ ከፋይናንስ ተቋማት እና ከግሉ ዘርፍ ጋር የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ትቅደም ወርቁ የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማኅበር የንግድ የልማት አገልግሎትን የበለጠ ለሴቶች ተደራሽ በማድረግ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና እና ዓለም አቀፍ የንግድ ትስስርን በአግባቡ ለመጠቀም፣ ነጋዴ ሴቶች የአካባቢያቸውን ምርት እና አገልግሎት ለማስተዋወቅ እንዲችሉ እየሠራ ነው ብለዋል። ነጋዴ ሴቶች ተወዳዳሪ እንዲኾኑ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ሴት ነጋዴዎች ለክልሉ እና ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ አወንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረከቱ ለማስቻል፣ መብት እና ጥቅማቸውን ለማስከበር አልሞ የሚሠራ ማኅበር ነው ብለዋል።
አሁን ላይ በ121 ከተሞች እና ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ከ151 ሺህ በላይ ሴቶችን ወክሎ እየሠራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
በዛሬው የምክክር መድረክ ባለፋት ሦሥት ዓመታት በተለያዩ ኢንተርፕራይዞች ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶች እና ወጣቶች ምን ያህል ውጤታማ እንደኾኑ፣ ያጋጠሟቸው ችግሮች፣ ለአምራቾች ብድር በማመቻቸት ረገድ የተጠና ጥናት መሠረት ተደርጎ ውይይት ተደርጎበት የመፍትሔ አቅጣጫ ይቀመጡበታል ተብሏል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም በክልሉ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ኢንተርፕራይዞች አውደ ርዕይ ያቀርባሉ ነው የተባለው።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!