ልጆች በዕድሜያቸው ማግኘት ያለባቸውን ዕውቀት እንዲያገኙ ሁሉም መተባበር አለበት።

9

ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ተማሪዎች ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡ የሰሜን ጎጃም ዞን ደግሞ ችግሩ ካለባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡

በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ አሚኮ ያነጋገራቸው የተማሪ ወላጅ በአካባቢያቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት ትምህርት ተቋርጦ በመቆየቱ ተማሪዎች ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን ነግረውናል።

በተለይ ሴት ተማሪዎች ያለዕድሜያቸው ወደ ትዳር እንደገቡ እና ከእርሳቸውም ልጆች አንዷ ተስፋ በመቁረጥ ወደ ትዳር እንደገባች ነው የነገሩን።

አሁን ላይ የትምህርት መቋረጥ ያስከተለውን ችግር በማየት ማኅበረሰቡ ተወያይቶ ልጆቹን እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል። ልጆች ከትምህርት ቤት በመቅረታቸው ተስፋ በመቁረጥ አልባሌ ቦታ እየዋሉ በመኾናቸው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አለመግባባት ውስጥ እንደገቡም አንስተዋል፡፡

እንደወላጅ ልጆች የተሻሉ እንዲኾኑ፣ ለሀገር ተተኪ የተማረ ትውልድ ለማፍራት፣ እራሳቸውን ለውጠው ቤተሰቦቻቸውን ብሎም ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ትምህርት አስፈላጊ ነው ብለዋል። ትምህርት ከፖለቲካ ነጻ ኾኖ ልጆች መማር አለባቸው ነው ያሉት።

ሦሥት ተማሪ ልጆች ያሏቸው በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ነዋሪ ትምህርት በተቋረጠባቸው ዓመታት የተማሪዎችም የወላጆችም ስሜት መጎዳቱን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በአካባቢያቸው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጀምሮ ሁለቱ ልጆቻቸው ትምህርት የጀመሩ ቢኾንም አሁንም አንዷ ልጃቸው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እንዳልጀመረች ገልጸዋል፡፡

በአካባቢያቸው ትምህርት እንዲከፈት ውይይቱ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡ በዚህም ተስፋ አለን ያሉት የተማሪ ወላጅ ሁሉም አካል ተባብሮ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የሰሜን አቸፈር ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የሽነው ወርቅነህ በወረዳው ባለፉት ሁለት ዓመታት በአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱን አንስተዋል።

በወረዳው ካሉት 77 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በ2017 የትምህርት ዘመን ሲያስተምሩ የቆዩት ሰባት ትምህርት ቤቶች ብቻ እንደነበሩ ገልጸዋል። በዚህ ደግሞ በርካታ ሕጻናት በተስፋ መቁረጥ ለተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

ለ2018 የትምህርት ዘመንም ከትምህርት መሪዎች ጋር ትምህርትን ወደነበረበት ለመመለስ ውይይት ተካሂዷል ብለዋል። በወረዳው መምህራን፣ ርእሰ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች በየቀጣናው የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የወላጆች እና መምህራን ኅብረት ኮሚቴ አባላት ከማኅበረሰቡ ጋር በመወያየት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል። በዚህም እስካሁን በ21 ትምህርት ቤቶች ትምህርት መጀመሩን ገልጸዋል።

በትምህርት ዘመን 90 ሺህ 672 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እስካሁን 15ሺህ 500 ተማሪዎች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡ አፈጻጸሙም ዝቅተኛ እና 17 በመቶ ነው፤ አሁንም የማወያየት ሥራው መቀጠሉን ተናግረዋል።

ትውልድን ለማነጽ ትምህርት አስፈላጊ ነው ያሉት ኀላፊው ከየትኛውም ተጽዕኖ ነጻ ኾኖ ልጆች እንዲማሩ ሁሉም የድርሻውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠይቀዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ነጋልኝ ተገኘ በዞኑ ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት ለማስጀመር ከማኅበረሰቡ ጋር በመወያየት በችግሮች ዙሪያ መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ካሉ 503 ትምህርት ቤቶች የተከፈቱት 172 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸውም ነው ያሉት፡፡

የተማሪ ምዝገባን በተመለከተ 496 ሺህ 864 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እስካሁን 108 ሺህ ተማሪዎች ብቻ ነው የተመዘገቡት፡፡ አፈጻጸሙም 22 በመቶ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ከባለፈው ዓመት የተወሰነ መሻሻል ቢኖርም አሁንም ገና በጅምር ላይ ያለ አፈጻጸም ነው ብለዋል፡፡

እንደዞን ማኅበረሰቡን የማወያየት ሥራው እና ምዝባው እንደቀጠለ ነው ብለዋል፡፡ ትምህርት ማኅበራዊ ተቋም ነው ያሉት ኀላፊው የተዘጉ ተቋማትን ማስጀመር የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል፤ ለዚህም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ትምህርት የሁሉም ነው፤ ሕጻናት የመማር መብት አላቸው ያሉት ኀላፊው ሕጻናት እንዲማሩ ወላጆች እና ማኅበረሰቡ ኀላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ቤቶች ነጻነታቸው ተከብሮ ከየትኛውም ተጽዕኖ ነጻ ኾነው ተማሪዎች እንዲማሩ ሁሉም መተባበር አለበት ብለዋል፡፡

ልጆች በዕድሜያቸው ማግኘት ያለባቸውን ዕውቀት እንዲያገኙ እና መምህራን በነጻነት ተንቀሳቅሰው ትውልድ እንዲቀርጹ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል እንዲተባበር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሃላባ እና ከምባታ ዞኖች የተገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮችን አስረከቡ። 
Next articleነጋዴ ሴቶች ተወዳዳሪ እንዲኾኑ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማኅበር አስታወቀ።