የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ከ950 ሺህ በላይ የጉልበት ሠራተኞችን እንደሚፈልግ የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ።

17
ባሕር ዳር: መስከረም 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሰብል ሰብሰባ ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞችን ከሚፈልጉ አካባቢዎች መካከል የምዕራብ ጎንደር ዞን አንደኛው ነው። የነጭ ወቅር ምድር እየተባለ የሚጠራው አካባቢው ሰሊጥ እና ሌሎች ሰብሎችን በስፋት በማምረት ይታወቃል።
በምርት ዘመኑ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ በርካታ የጉልበት ሠራተኞችን እንደሚፈልግ ዞኑ አስታውቋል።
አርሶ አደር ሀፍቱ ጽዱ ይባላሉ፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ በ343 ሄክታር መሬት ጥጥ፣ ሰሊጥ እና ማሽላ ማምረታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ200 ሄክታር መሬት በላይ የሚኾነው በሰሊጥ ምርት የተሸፈነ መኾኑን ገልጸዋል።
የሰብሉ ቁመና ሲታይ የሚጠብቁትን ያህል ምርት ሊያገኙ እንደሚችሉ የተናገሩት አርሶ አደር ሀፍቱ ይህንን ምርት ለመሰብሰብ እስከ 400 የሚደርሱ የጉልበት ሠራተኞች እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡
ለሠራተኞችም የተሟላ መጠለያ፣ ምግብ፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። ከተላላፊ እና ከወረርሽኝ በሽታዎች ለመከላከልም የጤና ባለሙያ በሥራቸው መኖሩን ተናግረዋል። ከበድ ያለ ሕመም ሲከሰትም ወደ ተሻለ ሕክምና በመላክ የጤንነታቸውን ሁኔታ እንደሚከታተሉ አስታውቀዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን በ2017/2018 ምርት ዘመን ከ525 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል፡፡ ከዚህም ከ12 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
በዘር ከተሸፈነው አጠቃላይ መሬት 182 ሺህ ሄክታር የሚጠጋው መሬት በሰሊጥ ምርት የተሸፈነ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ የሰሊጥ ሰብሉ ለአጨዳ የደርሰ በመኾኑ በዞኑ በሁሉም አካባቢ ምርቱ እየተሰበሰበ ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ምርት ከብክነት ነጻ በኾነ መንገድ ለመሰብሰብ ከ950 ሺህ በላይ የጉልበት ሠራተኞች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት። ሠራተኞች ወደ አካባቢው እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል።
ለአጨዳ የሚመጡ ሠራተኞችን ለመቀበልም በቂ የኾነ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ምግብ እና መኝታ ከሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች ጋር መቅረቡን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከተላላፊ እና ከወረርሽኝ በሽታዎች ለመከላከል የጤና ክላስተር በአደረጃጀት በማዘጋጀት የመከላከል ሥራ ይሠራል ነው ያሉት፡፡
በዞኑ የሚመረተው የሰሊጥ ምርት ለክልሉ ብቻ ሳይኾን እንደ ሀገር ፋይዳው የጎላ ነው ያሉት ኀላፊው ሰብሉ የሀገራችን የውጭ ምንዛሬ ችግር የምንቀርፍበት ነው ብለዋል።
በየደረጃው ያሉ ሁሉም አካላት ሰብሉ ከብክነት ነጻ በኾነ መንገድ እንዲሰበሰብ የበኩላቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየቦሌ ክፍለ ከተማ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ ጀመረ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሃላባ እና ከምባታ ዞኖች የተገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮችን አስረከቡ።