ለማዕድን ልማት ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ ነው።

6
ደብረ ማርቆስ፡ መስከረም 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከግንባታ እስከ ኢንዱስትሪ ማዕድናት ሰፊ ፀጋዎች አሉ።
በዞኑ የብረት እና ለኀይል አገልግሎት የሚውሉ ማዕድናት ይገኛሉ። ለአብነትም እንደ ሊትየም፣ የድንጋይ ከሰል፣ እምነ በረድ፣ ግራናይት፣ ላይም ስቶን፣ ጅፕሰም፣ ኮፐር፣ ባዛልት አሸዋ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
በደጀን ወረዳ የሚገኘው የበልስቲ ኢንዱስትሪያል ታይም ጂፕሰም ፋብሪካ ሥራ አሥኪያጅ ታደሰ በሪሁን ፋብሪካው በቀን ከ24 ሺህ በላይ ምርቶችን እንደሚያመርት ገልጸዋል።
የፀጥታ ችግሩ ግብዓቶችን በሚፈለገው ልክ ለማቅረብ ተጽዕኖ ቢያሳድርባቸውም ፋብሪካው ከ300 በላይ የሚኾኑ ሠራተኞችን አደራጅቶ እየሠራ መኾኑንም ሥራ አሥኪያጁ ተናግረዋል።
በአካባቢው በተለይ በዓባይ ሸለቆ ዙሪያ የላይም ስቶን እና ጂፕሰምን የመሳሰሉ ማዕድናት ለኢንዱስትሪ እና ግንባታ ዘርፉ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለመድረግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የደጀን ወረዳ ማዕድን ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዋልተንጉስ አዱኛው በወረዳው የሚገኙ እንደ ድንጋይ ከሰል፣ የፍል ውኃ እና የወርቅ ማዕድናትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለሃብቶች ወደ አካባቢው በመምጣት እንዲያለሙ የጽሕፈት ቤት ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ማዕድን ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ የሻረግ መልሰው ዞኑ ለግንባታ እና ኢንዱስትሪዎች ግብዓት መኾን የሚችሉ የተለያዩ የማዕድን ፀጋዎች የታደለ መኾኑን ገልጸዋል።
ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ ፋብሪካዎችን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም ኀላፊዋ ጠቁመዋል፡፡ የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ማምረት እንዲገባ መደረጉንም ለአብነት አንስተዋል።
በዞኑ የሚገኙ የጅፕሰም ፋብሪካዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ያሉት ኀላፊዋ የበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
ዘርፉ ማመንጨት የሚገባውን ኢኮኖሚ እንዲያመነጭ እና ለሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ነው የገለጹት።
በማዕድን ዘርፍ ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ያልገቡ ባለሃብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article700 ታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
Next articleአረጋውያን በምንም ነገር የማይተመኑ የሀገር ባለውለታዎች በመኾናቸው እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል።