ችሎት ላይ ያለን ሥነ ሥርዓት ምን ያህል ያውቃሉ?

13

ባሕር ዳር: መስከረም 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ፍርድ ቤቶች የዜጎች የመጨረሻ የመብት ማስከበሪያ ናቸው። ፍርድ ቤቶች በሕግ አውጭው አካል አስቀድመው የወጡ ሕጎችን የመተረጎም ሥልጣን የተሰጣቸው ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች ተግባራቸውን ከሚያከናውኑባቸው ሥርዓታት መካከል ደግሞ ችሎት አንዱ ነው።
ችሎት የሚመራበት የራሱ የኾነ ሥነ ሥርዓት አለው። ፍርድ ቤቶች እንደማንኛውም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ቢኾኑም ባለጉዳዮች ሲቀርቡ ሊከተሏቸው የሚገቡ ሥነ ሥርዓት አሏቸው፡፡ የችሎት ሥነ ሥርዓት ዓላማ ፍርድ ቤቶች የፍርድ አሰጣጥ ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን ሲባል የሚከበሩ ናቸው፡፡

ፍርድ ቤቶች በወንጀል እና በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ክርክር በሚደረግበት ችሎት ከሚሳተፉ ዋና ዋና ተዋንያን መካከል ዳኞች፣ ከሳሽ፣ ተከሳሽ፣ ቃቤ ሕግ፣ ጠበቆች፣ ምስክሮች፣ ችሎት ጸሐፊዎች፣ ችሎት አስከባሪዎች፣ ችሎት ተከታታዮች እና ሚዲያ ይገኙበታል፡፡

👉 ችሎት ላይ በተሳታፊዎች የሚጠበቁ የሥነ ሥርዓት ጉዳዮች፡
የአሚኮ የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር አብዬ ካሳሁን በችሎት ወቅት የችሎት ተሳታፊዎች ሊያከብሯቸው የሚገቡ ሥነ ሥርዓታት መኖራቸውን ያብራራሉ።
👉 የአለባበስ ሥነ ሥርዓት፡- ዳኞች፣ ዐቃቢያነ ሕጎች እና ጠበቆች ወደ ችሎት በሚገቡበት ወቅት ካባ የመልበስ ግዴታ እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡ ማንኛውም ሰው ፊት እና ዓይኑን ሙሉ ለሙሉ የሚሸፍን ወይም ሰው እንዳያየው የሚያደርግ ልብስ ለብሶ ችሎት መግባት እንደሌለበትም አስረድተዋል፡፡
በሃይማኖት ወይም በባሕል ምክንያት የሚለበሱ ልብሶችን ለብሶ ችሎት መግባት የተፈቀደ ነው፡፡ ኾኖም ችሎቱ የዚህን ሰው ማንነት ለማጣራት ወይም ለማረጋገጥ ሲል የዚያን ሰው ክብር፣ ባሕል እና ሃይማኖት በማይጋፋ መልኩ ልብሱን ከላዩ ላይ እንዲያነሳ ማዘዝ ይችላል፡፡
👉 ለችሎት ክብር ስለመቆም፡- በችሎት ሂደት ፍርድ፣ ቅጣት፣ ውሳኔ፣ ብይን ሲነበብ፣ የክስ እና መልስ ቅብብል ሲደርግ፣ ክርክር ሲካሄድ፣ ባለጉዳዩ ምስክሮችን ሲያሰማ፣ አቤቱታ ሲያቀርብ፣ ትዕዛዝ ሲሰጥ፣ ውሳኔ ሲነበብ ወይም ዳኛው በያዘው ጉዳይ በሚያስችልበት ወቅት የሚመለከተው ባለጉዳይ ቆሞ መከታተል እንደሚኖርበት አስረድተዋል፡፡
ማንኛውም የፍርድ ቤቱ ሠራተኛ፣ ፖሊስ፣ የችሎቱ ተገልጋይ፣ ተከራካሪ ወይም ባለጉዳይ በሚከተሉት ሁኔታዎች እራሱን ዝቅ በማድረግ ለችሎቱ ያለውን ክብር ሊያሳይ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ አብዬ ማብራሪያ ዳኞች ወደ ችሎት ሲገቡ እና ችሎት አልቆ በሚወጡበት ጊዜ መነሳት በችሎት ውስጥ ካለው ሰው ሁሉ የሚጠበቅ ሥነ ሥርዓት ነው። የመነሳቱ ትርጉምም ለፍትሕ የሚሰጠው ክብር መኾኑንም አንስተዋል፡፡
👉 የስም አጠራር ሥነ ሥርዓት፡ ዳኞችን፣ ጠበቆችን፣ ምስክሮችን ሲጠሩ ትክክለኛውን ማዕረጋቸውን በመጥራት መኾን አለበት፡፡ በችሎት ውስጥ ለማንኛውም ለሴት ዳኛ ክብርት ዳኛ፣ ለወንድ ዳኛ ክቡር ዳኛ፣ የተከበረው ፍርድ ቤት በማለት መጥራት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡
👉 ለማንኛውም ሰው በችሎቱ የተከለከሉ ጉዳዮች:
አቶ አብዬ እንደገለጹት በችሎት ውስጥ ድምጽ ከፍ በማድረግ መናገር ወይም መንጫጫት፣ ጎኑ ካለው ወይም ከሌላ ሰው ጋር ማውራት፤ በሞባይል መነጋገር የተከለከለ ነው።
በችሎት ውስጥ ሲጋራ ማጨስ፣ ቃጠሎ የሚፈጥሩ መሳሪያዎችን ይዞ መግባት፣ በድምጽ፣ በምልክት ወይም በማንኛውም ሁኔታ ችሎቱን ማወክ ወይም ለክርክሩ አስፈላጊ ያልኾነውን ድርጊት ወይም ንግግር ማድረግ፣ የተከለከለ መኾኑንም አመላክተዋል።
የሰውን ስሜት የሚስብ እና የሚነካ ተግባር መፈጸም፣ መጠጣት፣ መመገብ፣ ጫት መቃም፣ ማስቲካ ማኘክ፣ መተኛት የመሳሰሉት ነገሮችም የማይፈቀዱ መኾናቸውን አንስተዋል።
ዳኛው ወደ ችሎት ሲገባ እና ሲወጣ፣ የችሎቱን ትዕዛዝ፣ ብይን፣ ፍርድ እና ውሳኔ አንብቦ ከጨረሰ በኋላ በጉዳዩ ላይ ክርክር ማንሳት ወይም ስሜታዊ በኾነ ሁኔታ አቋምን መግለጽ የተከለከለ ነው፡፡
የዳኛ ፈቃድ ሳይኖር ጠበቃ ተጠርጣሪውን ወይም ተከሳሹን ማነጋገር፣ የጦር መሳሪያ፣ ዱላ ወይም ስለታማ የኾኑ መሳሪያዎችን መያዝ እንደማይቻልም ገልጸዋል።
እንደ አቶ አብዬ ማብራሪያ ሥልጣን ካለው አካል ፍቃድ ሳይኖረው በሞባይል፣ በካሜራ ወይም በቪዲዮ ፎቶ ማንሳት፣ ድምጽ መቅዳት፣ ሻንጣ፣ ፌስታል እና ትላልቅ ቦርሳዎች ወይም ለችሎቱ ሥነ ሥርዓት የማይመች ድምጽ መፍጠር የሚችሉ ማንኛውንም እቃዎች ይዞ ወደ ችሎቱ መግባት አይቻልም።
👉 በችሎት ወቅት ሥነ ሥርዓትን አለማክበር የሚያስከትለው ተጠያቂነት
የችሎቱን ሥነ ሥርዓት በጣሰው ማንኛውም ሰው ላይ የችሎቱ ዳኛ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ችሎቱ እንዳይገባ መከልከል፣ ከችሎቱ ክፍል እንዲወጣ ማድረግ እንደሚችል አብራርተዋል።
በወንጀል እና በፍትሐ ብሔር ሕግ መሠረት የችሎቱን ሥርዓት በመጣስ፣ በማወክ ወይም በማደናቀፍ ወንጀል ወዲያውኑ ፍርድ መስጠት እና ቅጣት መወሰን እንደሚያስችልም አንስተዋል።
የወንጀል ሕግ አንቀጽ 449 እንደተቀመጠው በፍርድ ቤት ምርመራ በሚከናወንበት ጊዜ የዳኝነት ሥራውን በማከናወን ላይ ያለውን ዳኛ ወይም ፍርድ ቤትን በማናቸውም መንገድ በመስደበ፣ በማወክ፣ በማፌዝ፣ በመዛት በሌላ መንገድ ያወከ እንደሆነ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከሦሥት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ያስቀጣል ነው ያሉት።
አንድ ተከራካሪ ወገን በፍርድ ቤት ቀርቦ እውነት እንዲናገር ታዝዞ በፍርድ ቤት በሚወሰን ጭብጥ ላይ አግባብነት ያላቸውን ፍሬ ነገሮች በሚመለከት እያወቀ ሐሰተኛ ቃል የሰጠ እንደኾነ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ያስቀጣል ብለዋል።
ሐሰተኛውን ቃል የሰጠው የወንጀል ክስ ሂደት ላይ ኾኖ ኢ ፍትሐዊ ውሳኔ ሊያስከትል የሚችል እንደኾነ ከሦሥት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል ነው ያሉት፡፡
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 452 እንደተቀመጠው ተከራካሪው ምሎ ወይም ማረጋገጫ ሰጥቶ እንደኾነ በተለይ ደግሞ የተፈለገው ውጤት በከፊል ተገኝቶ እንደሆነ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት የማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል ብለዋል።
በወንጀል ሕግ አንቀጽ 453 ንዑስ አንቀጽ 1 እንደተገለጸው ሐሰተኛ ምስክርነት ወይም ሐሰተኛ አስተያየት ወይም ትርጉም መስጠትም በሀገራችን የወንጀል ሕግ ቀላል እስራት ወይም ነገሩ ከባድ በኾነ ጊዜ ደግሞ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡
ምስክሩ ምሎ ወይም ማረጋገጫ ሰጥቶ ከኾነ በተለይም የተፈለገው ውጤት በከፊል ወይም በሙሉ ተገኝቶ እንደኾነ ቅጣቱ ከአስር ዓመት የማይበልጥ ጽኑ እሥራት እንደሚኾን ነው የገለጹት፡፡
የፍርድ ቤቱ ዳኞች እና ሠራተኞች ኾነው በችሎት ሂደቱ ላይ የሚሳተፉት ከኾኑ ጥፋታቸው በአሥተዳደራዊ መንገድ በዲስፕሊን ጭምር የሚያስጠይቅበት አግባብ እንደሚኖር ነው ያብራሩት፡፡
ኀላፊነቱን በአግባቡ ያልተወጣ የፍርድ ችሎት ተሳታፊ ልዩ ልዩ ተጠያቂነት ያለበት መኾኑን ተገንዝቦ የፍትሕ አሰጣጥ ሂደቱን መደገፍ ይገባዋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበበጀት ዓመቱ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ወጋገን ባንክ አስታወቀ።
Next articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልዕክት