የዓሣ ሃብትን ለማሳደግ ምን እየተሠራ ነው?

6
ባሕር ዳር: መስከረም 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ ጣና ሐይቅ አካባቢ ካሉ የዓሣ ሬስቶራንቶች በአንዱ አሚኮ ያገኛቸው መምህርት ሻሽቱ ዓለማየሁ ከጎንደር ከተማ ልጆቻቸውን ሊጎበኙ በተደጋጋሚ ወደ ባሕር ዳር እንደሚመጡ እና በዚሁ አጋጣሚም ዓሣ የመመገብ ልማድ እንዳላቸው አጫውተውናል።
መምህርቷ “ሁሌም ወደ ባሕር ዳር ሳቀና አሣ ሳልመገብ አልመለስም” ይላሉ፡፡ እኛም ያገኘናቸው እንደተለመደው ከልጆቻቸው ጋር ዓሣ ለመመገብ መጥተው ነው።
በሐይቁ ዳርቻ እየተዝናኑ መመገብ የመንፈስ እርካታ ቢኖረውም አሁን ላይ ዋጋው በመወደዱ ምክንያት ወደ ቤት ለመውሰድ እንደተገደዱ ጠቁመዋል፡፡
በዓሣ ሬስቶራንቱ አሚኮ ያገኛቸው አቶ አንተነህ መላኩ በሥራ ምክንያት ባሕር ዳር መኖር ከጀመሩ ረጅም ጊዜ እንደኾናቸው እና ከሌሎች ምግቦች በተለየ ዓሣ መመገብን ምርጫቸው እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት፡፡
ቀደም ሲል የዓሣ ነጋዴዎች በየሰፈሩ ይዘው በመዞር እንደለፈለጉ ያገኙ የነበረ ሲኾን አሁን ላይ እንደልብ እንደማይገኝ እና ዋጋውም እንደተወደደ ይናገራሉ፡፡
ዛሬም ቤት ላይ ሠርቶ ለማስተናገድ በቅርበት ባለመገኘቱ ከእንግዳቸው ጋር ዓሣ ለመገባበዝ ወደ ሐይቁ ዳርቻ እንደመጡ ተናግረዋል፡፡
አቶ አንተነህ ዓሣ ከጤንነት አንጻር የሚሰጠው ጥቅም ቀላል ባለመኾኑ እና በኅብረተሰቡ ዘንድም ያለው ተፈላጊነት ከፍተኛ በመኾኑ ምርቱ በስፋት የሚመረትበት መንገድ ቢኖር እና የዋጋ መሻሻልም ቢደረግ መልካም ነው ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ በዓባይ ወንዝ ዳር በተቀናጀ የግብርና ሥራ የተሰማራው ወጣት አይሸሽም ዓለሙ የግብርና ሥራን ከልጅነቱ ጀምሮ ከቤተሰብ ጋር ሢሠራ ማደጉን ይናገራል።
አሁንም ከ600 ካሬ ባላነሰ መሬት ላይ የውኃ ገንዳ በመገንባት እና ውኃ በመሙላት ዓሣ የማምረት ሥራ መጀመሩን ገልጿል።
ዓሣ ለማምረት ያነሳሳውን ምክንያት ሲያስረዳ ዓሣ ለመመገብ ወደ ዓሣ ቤቶች ጎራ ያለበት አጋጣሚ እንደኾነ ገልጿል።
ዓሣን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ለማድረስ በሚል ባለው ቦታ ሥራ ለመጀመር መነሳቱንም ይናገራል።
ለዚህ ሥራ የባሕር ዳር ከተማ እንስሳት እና ዓሣ ሃብት መምሪያ ከውኃ ገንዳ ግንባታው ጀምሮ የሚራቡ የዓሣ ጫጩቶችን ወደ ኩሬው በመጨመር እና ምክረ ሃሳቦችን በመስጠት ድጋፍ እንዳደረገለት ገልጿል።
ወደ ሥራ ሲገባም 6ሺህ 500 የዓሣ ጫጩቶች ወደ ገንዳ ውኃው መጨመሩን አስታውሷል። ወጣት አይሸሽም አሁን ላይ የዓሣ ጫጩቶቹ አድገው እና ተራብተው በአማካይ ከ10ሺህ እስከ 15ሺህ ሊደርሱ እንደሚችሉ ተናግሯል።
በቀጣይ በካሬ ከታጠረ ገንዳ በመውጣት እና ወንዙን በመጠቀም ዓሣን በስፋት በማምረት እና ዘመናዊ የዓሣ ሬስቶራንት በመክፈት ለማኅበረሰቡ ግልጋሎት ለመስጠት አቅዶ እየሠራ መኾኑንም ተናግሯል።
እስካሁን ባለው በሥሩ ለዘጠኝ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ነው ወጣቱ ያብራራው።
ወጣት አይሸሽም እንዳለው ኢትዮጵያ ብዙ ወንዞች እና ሐይቆች፣ ለም አፈር እና ምቹ የአየር ንብረት ባለቤት በመኾኗ ይህንን ዕድል ተጠቅሞ በአካባቢው በሚገኙ ትንንሽ መሬቶች የውኃ ኩሬ በመፍጠር የዓሳ ምርትን ጨምሮ ሌሎች ልማቶችን ለማልማት እየሠራ ነው።
ወጣቱ የዓሣ ምርትን በማምረት የራሱን የምግብ ፍላጎት አሟልቶ ሀገሩንም መጥቀም እንዳለበት ነው አስተያየቱን የገለጸው።
በወጣት አይሸሽም ዓለሙ አማካኝነት የሥራ ዕድል ተፈጥሮላት ተጠቃሚ እንደኾነች የተናገረችው ወጣት በላይነሽ ሹመት የሥራ ዕድል ከማግኘቷ በፊት በችግር ውስጥ እንደነበረች ጠቁማለች።
አሁን ግን በተፈጠረላት የሥራ መስክ በሚከፈላት የወር ደመወዝ የሚያስፈልጋትን ማሟላት እንደቻለች ተናግራለች። በዚህም የነበረባትን ችግር መፍታት እንደቻለች ነው ያስረዳችው፡፡
የዓሣ ሃብትን በማሳደግ የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላት እየተሠራ መኾኑን የክልሉ እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ቢሮ አስታውቋል፡፡
ቢሮው እየቀነሰ መጣውን የዓሳ ሃብት ለማሳደግ እና የኅብረተሰቡን የዓሳ ፍላጎት ለማሟላት የምርምር እና ብዜት አቅሙን በማሳደግ ብዛት ያላቸውን የዓሣ ጫጩቶችን በማባዛት ወደ ጣና እና ሌሎች ውኃማ አካላት እየጨመረ ይገኛል፡፡
ይህንን ሥራ ለማጠናከርም ባለፈው ዓመት 900ሺህ የዓሣ ጫጩቶችን ለማሰራጨት አቅዶ 775 ሺህ የሚደርሱ የዓሣ ጫጩቶች ወደተለያዩ የውኃ አካል መሰራጨታቸውን የክልሉ እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ የዓሣ ቴክኖሎጅ ባለሙያ አበበ ፈንታሁን ተናግረዋል።
ቢሮው በዋናነት የተፈጥሮ የውኃ አካላት ላይ የሚመረተው የዓሣ ምርት ዘላቂ እንዲኾን የማድረግ እና ጥበቃዎችን የማካሄድ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።
የውኃ አማራጭ ያላቸውን አርሶ አደሮች በዓሣ ግብርና እንዲሳተፉ የማድረግ እና ኩሬ ካዘጋጁ በኋላ ለኩሬው ተስማሚ የኾነ የዓሣ ጫጩት በመጨመር የምርቱ ተጠቃሚ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ምርት የማይሰጡ ለተለያዩ አላማዎች ተብለው የተገነቡ ግድቦች ላይም ተስማሚውን የዓሣ ጫጩት በመጨመር የዓሳ ምርት እንዲያስገኙ የማድረግ እና ከተለያዩ የውኃ አካላት የሚመረተውን የዓሣ ምርት ጥራቱን ጠብቆ ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ የማድረግ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
በዚህም ጫጩት የሚያስፈልጋቸው ወደ 43 የሚደርሱ ግድቦች መለየታቸውንም ተናግረዋል።
በእነዚህ እና በተፈጥሮ የውኃ አካለት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚኾኑ የዓሣ ጫጩቶችንም ለማሰራጨት ከባሕር ዳር ዓሣ እና ሌሎች የውኃ ውስጥ ምርምር ጋር የማባዛት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ባለሙያው ተናግረዋል።
በሐምሌ 2017 ዓ.ም እና በነሐሴ 2017 ዓ.ም ብቻ ወደ 80ሺህ የሚኾኑ ጫጩቶችንም ወደ ተለያዩ የውኃ አካላት ማሰራጨት መቻሉን ባለሙያው አብራርተዋል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ጣና ሐይቅ ላይ ብቻ በአንድ ዓመት እስከ 20 ሺህ ቶን አካባቢ የዓሣ ምርት ማምረት ይቻላል፡፡ ቢሮውም ይህንን ታሳቢ ያደረገ 325 ሺህ የሚኾኑ የቀረሶ ዓሣ ጫጩቶችን አባዝቶ ወደ ሐይቁ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
ዓሣ ከዚህ በፊት በተፈጥሮ ሐይቆች ብቻ ነበር የሚመረተው ያሉት ባለሙያው አሁን ላይ በክልሉ በየትኛውም ቦታ በተለያዩ ግድቦች እና በአርሶ አደሮች ኩሬ እየተመረተ ለማኅበረሰቡ እየቀረበ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ በዚህም ማኅበረሰቡ ዓሣ የመመገብ ባሕሉ እየዳበረ መጥቷል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዘርፉ 29 ሺህ የሚኾኑ ወጣቶች በዓሣ ምርት እና ከዓሣ ጋር በተገናኙ ሥራዎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች ኾነዋል ብለዋል፡፡
ከዓሣ ፍላጎት አንጻር የሚታዩ እጥረቶችን ለመቅረፍ ቢሮው ለተለያዩ ዓላማዎች ተብለው የሚገነቡ ግድቦች ወደ ዓሣ ማምረት እንዲገቡ በማድረግ በሁሉም ዞኖች የዓሣ ምርት እንዲገኝ እየተሠራ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም በክልሉ ያሉ የውኃ አካላትን በሙሉ በመጠቀም አርሶ አደሮችን በዓሣ ምርት ማምረት ሥራ እንዲሳተፉ በማድረግ እና በተፈጥሮ የውኃ አካላት ላይ ያለው የዓሣ ምርትም ዘላቂ እንዲኾን የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይሠራል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleወጣቶችን በተለያዩ መስኮች ለማብቃት እና ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው።
Next articleየክልሉ መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪው የተለየ ትኩረት ሰጥቶታል።