
ደብረ ብርሃን: መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ ማጠቃለያ እውቅና እና የ2018 በጀት ዓመት የበጋ በጎ ፈቃድ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በ2017 በጀት ዓመት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በደብረ ብርሃን ከተማ ከ92 ሺህ በላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ የታቀደ ቢኾንም በተሠራው የንቅናቄ ተግባር ከ129 ሺህ በላይ ሰዎችን ማሳተፍ መቻሉን የተናገሩት የከተማ አሥተዳደሩ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አውራሪስ አረጋ ናቸው።
“በተሠራው ሥራም ከ128 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ሃብት ማዳን መቻሉን” ተናግረዋል።
የአረጋውያን ቤት ጥገና፣ የደም ልገሳ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት እና ሌሎች ተግባራት ላይ ወጣቶች መሳተፋቸውንም አንስተዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባሕል እየኾነ በመምጣቱ የከተማው ነዋሪዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚነታቸው ማደግ ችሏል ያሉት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ናቸው።
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተሠራው ተግባር በመንግሥት ሃብት መከናወን የማይቻሉ በርካታ የልማት ሥራዎች በመከናወናቸው ነዋሪዎች ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዲያገኙ አስችሏል ነው ያሉት።
በሂደቱ ተሳታፊ ለነበሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ምስጋና አቅርበዋል። በ2018 የበጋ በጎ ፈቃድ ሥራዎች በንቅናቄ ሊተገበር እንደሚገባም በዕለቱ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ዮናስ ታደሰ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
