
ሰቆጣ: መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአጋዥ ድርጅቶች እና በመልሶ ማቋቋሚያ መርሐ ግብር አምስት ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።
16 ትምህርት ቤቶች በዳስ የሚገኙ ሲኾን በአጋዥ ድርጅቶች እና በመልሶ ማቋቋሚያ መርሐ ግብር አምስት ትምህርት ቤቶች ተገንበተው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን ነው የተገለጸው።
ተማሪ አዲሴ አበባው ይባላል በድሃና ወረዳ 19 ቀበሌ የጎመንጌ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ተማሪ የነበረ ሲኾን ትምህርት ቤቱ ለመማር ምቹ ባለመኾኑ ከትምህርት ገበታ እርቆ እንደነበረ ከአሚኮ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።
በዳስ እና ለመናድ በተዘጋጀ ክፍል ስማር ከአሁን አሁን ይደረመሣል በሚል ምክንያት ትምህርቴን አቋርጨ ነበር የሚለው ተማሪ አዲሴ በዚህ ዓመት ትምህርት ቤቱ ደረጃውን ጠብቆ በመገንባቱ ያቋረጥኩትን ትምህርት ጀምሬለሁ ብሏል።
በማኅበረሰቡ አቅም በተደጋጋሚ ቢገነባም በአካባቢው ነፋስ እና በዝናብ ብዛት የተነሳ በየዓመቱ እየፈረሰ ያስቸግር እንደነበረ ወይዘሮ አለማየሁ ማሞ ያስታውሳሉ።
ልጅን ማስተማር እና የተገነቡ ክፍሎችን እንዳይጎዱ መጠበቅ የቀበሌዋ ሕዝብ ኀላፊነት ነው ብለዋል። ኀላፊነታችንንም እንወጣለን ነው ያሉት።
በዋግ ኽምራ ባሉ አራት ወረዳዎች 16 የመማሪያ ክፍሎችን የያዙ ስድስት ሕንጻዎችን ከስፖንሰር ሽፕ በተገኘ የ25 ሚሊየን ብር ድጋፍ ገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ የሴቭ ዘችልድረን ሰቆጣ ቅርንጫፍ ዋና ዳይሬክተር ምህረቱ ሞላ ናቸው።
በቀጣይም በዝቋላ ወረዳ እና በድሃና ወረዳ ያሉ ሁለት የዳስ ትምህርት ቤቶችን ወደ ክላስ ለመቀየር በዝግጅት ላይ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
በዋግ ኽምራ 16 ትምህርት ቤቶች በዳስ የሚገኙ ሲኾን በአጋዥ ድርጅቶች እና በመልሶ ማቋቋሚያ መርሐ ግብር አምስት ትምህርት ቤቶች ተገንበተው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኅላፊ ሰይፉ ሞገስ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት በዚህ በኩል ያበረከተው አስተዋጾኦ ከፍተኛ ነው ያሉት ኀላፊው በቀጣይም ቀሪ 11 ትምህርት ቤቶችን ወደ ክላስ ለመቀየር እና በክላስ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ስታንዳርድ ከፍ ለማድረግ እንሠራለን ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!