
ከሚሴ: መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጉባኤው የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀምን በመገምገም እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ላይ በመወያየት ያፀድቃል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋጡማ ሞላ በብሔረሰብ አሥተዳደሩም በ2017 በጀት ዓመት በሰላም እና በልማት ሥራዎች በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በ2017 በጀት ዓመት የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል የነበሩ ውስንነቶችን ለማረም ምክር ቤቱ ኀላፊነቱን ለመወጣትም ይሠራል ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ በ2017 በጀት ዓመት ለሰላም ትኩረት በመስጠት በተሠራው የተቀናጀ ሥራ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አንፃራዊ ሰላም መፈጠሩን ገልጸዋል።
የሕዝቡን የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታትም በተደረገው ጥረት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ223 በላይ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት መደረጉን ጠቅሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም የማኅበረሰቡን የሰላም፣ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በቅንጅት ይሠራል ብለዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል አስፈፃሚው አካል የሚሠራቸውን የሰላምና የልማት እንዲኹም የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች በየጊዜው በመገምገም ኀላፊነታቸውን እየተወጡ መኾኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የሕዝብ የእንደራሴነታችንን ኀላፊነት ለመወጣት በትኩረት እንሠራለን ብለዋል።
በጉባኤው የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የ2018 በጀት 3 ቢሊየን 485 ሚሊየን 858ሺህ 365 ኾኖ ጸድቋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን