ባለሃብቶች ወደ አማራ ክልል መጥተው እንዲያለሙ ጥሪ ቀረበ።

3
ባሕር ዳር: መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የራቫል ብረታ ብረት ማምረቻ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ እና በባሕር ዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኙ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የሥራ እንቅስቃሴ ታይቷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዝናቡ ይርጋ የባሕር ዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በሀገር ደረጃ ካሉት 21 የኢኮኖሚ ዞኖች መካከል አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ የተሟላ መሠረተ ልማቶች ያሉበት ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢኮኖሚ ዞኑ ገብተው በሥፋት አንዲያለሙ ይፈለጋል ብለዋል። ለዚህም አሳሪ የነበሩ አሠራሮችን መንግሥት ማሻሻሉን አንስተዋል።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽንም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ክትትል በማድረግ እና በመፍታት ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል። በኢኮኖሚ ዞኖች የሚያግጥሙ የኃይል አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ኢንቨስትመንት ያለሰላም አይታሰብም ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ባሕር ዳር ምቹ የኢንቨስትመንት አከባቢ መኾኗን ገልጸዋል። ኢንቨስትመንትን የሚያደናቅፍ ምንም ነገር የለም ነው ያሉት።
ባለሃብቶች በሩቅ የሚሰሙትን ያልተገባ መረጃ በመተው እና መጥተው በተጨባጭ በማረጋገጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በ25 ዓመቱ አሻጋሪ የልማት እቅዱ ላይ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አምራች ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት በዘርፉ ሲነሱ የነበሩ ማነቆዎችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመነጋገር ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተሠራ ስለመኾኑም አንስተዋል።
በጉብኝቱ የተሻለ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መመልከታቸውንም ተናግረዋል። በፈተና ውስጥም ኾነው ምርት እያመረቱ ለውጭ እና ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረቡ ያሉ ባለሃብቶችም በርካታ መኾናቸውን አንስተዋል።
በኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ ወደ ሥራ ያልገቡ ሼዶች መኖራቸውን ገልጸው ችግሮቻቸውን በመለየት ወደ ሥራ እንዲገቡ የክልሉ መንግሥት እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በጋራ እንደሚሠሩ አመላክተዋል።
ኢንቨስትመንት ሰላም እና የተረጋጋ አካባቢን ይፈልጋል ብለዋል። የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱንም አንስተዋል። ይህንን ተከትሎም በክልሉ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግሥት ለኢንቨስተሮች እና ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። በበጀት ዓመቱ ከ486 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶችን ለመሳብ በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
አማራ ክልል ያልተነካ የኢንቨስትመንት ጸጋዎች ያሉበት ክልል መኾኑን ያስረዱት አቶ እንድሪስ የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየተቀናጀ የፖሊዮ ወረርሽኝ የዘመቻ ክትባት ሊሠጥ ነው።
Next article“መንግሥት የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫዎችን ለማዘመን እና ለማስፋፋት ይሠራል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ