የተቀናጀ የፖሊዮ ወረርሽኝ የዘመቻ ክትባት ሊሠጥ ነው።

2
ባሕር ዳር: መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፖሊዮ በሽታ ሕጻናትን ለከፍተኛ የአካል ጉዳት ብሎም ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡ የበሽታው ዋነኛ መከላከያ ደግሞ ክትባት ነው፡፡
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ3ኛው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ የዘመቻ ክትባትን ለማካሄድ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በባሕ ዳር ከተማ አካሂዷል፡፡
የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በክልላችን ውስጥ በደቡብ ጎንደር ዞን እና ጎንደር ከተማ አሥተዳደር በሽታው ተገኝቷል ብለዋል። በሽታውን ለመከላከልም በዘመቻ ክትባቱን መስጠት አስፈላጊ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ደቡብ ጎንደር ዞን፣ ጎንደር ከተማ አሥተዳደር እና በሽታው ባልተከሰተባቸው አጎራባች ዞኖች ማለትም ምስራቅ ጎጃም፣ ሰሜን ጎጃም እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች፣ በባሕር ዳር ከተማ፣ በደብረ ታቦር ከተማ እና ደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደሮች ላይ ክትባቱ ይሰጣል ብለዋል።
የመድረኩ ዓላማ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ወስደው ለክትባት ዘመቻው መሳካት እንዲሠሩ ለማስቻል እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡
እንደ ሀገር ከ8 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ እና በክልላችን ደግሞ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የኾኑ ሕጻናት በክትባት ዘመቻው ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል፡፡ የክትባት ዘመቻው ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድም ነው የገለጹት።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ክፍል አሥተባባሪ ተሰማ በሬ የአሁኑ ክትባት በተገኙ የፖሊዮ በሽታዎች መሠረት የታወጀ ዘመቻ ነው ብለዋል፡፡ ክትባቱ ቤት ለቤት የሚሰጥ በመኾኑ ከዚህ በፊት ክትባት ያልወሰዱ ሕጻናት ሌሎች ክትባቶችንም እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም መደበኛ ክትባቱን ያልወሰዱትን እና ያቋረጡትን ሕጻናት ተቀናጅቶ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ኩፍኝ እና ትክትክ የመሳሰሉ ወረርሽኞች ተከስተው በዘመቻ ክትባት መሰጠቱን አስታውሰዋል። በዚህ ዘመቻም ተቀናጅቶ ይሠራል ብለዋል፡፡
እንደ ክልል ለክትባቱ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ያሉት አሥተባባሪው ማኅበረሰቡ፣ የጤና ባለሙያዎች እና መገናኛ ብዙሃን ቀኑ ሳያልፍ ሕጻናት እንዲከተቡ ርብርብ እንዲያደረጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አሚኮ ያነጋገራቸው የመድረኩ ተሳታፊ የሃይማኖት አባት አባ ታምራት ሀብቴ እንደ ሃይማኖት አባት ምዕመናን በተለይም እናቶች ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ ትምህርት እንሰጣለን ብለዋል፡፡
ሌላዋ ተሳታፊ የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር እንዬ ገነቱ የሕጻናት ክትባት ለእናቶች ቅርብ ነው ብለዋል፡፡ አብዛኞቹ ከእናቶቻቸው ጋር የሚውሉ ሕጻናት ናቸው የሚከተቡት ያሉት ዳይሬክተሯ እንደ ሴት አደረጃጀት የክትባቱን አስፈላጊነት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በመሥራት ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ የተሻለ ሥራ ሠርታለች።
Next articleባለሃብቶች ወደ አማራ ክልል መጥተው እንዲያለሙ ጥሪ ቀረበ።