መምህራን ትውልድ ቀራጮች ብቻ ሳይኾኑ የሀገር “አርክቴክቶችም” ናቸው።

1
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቀደመው ዘመን መምህራን በቀደመው ጊዜ የኀብረተሰብ ክፍል ዘንድ የተለየ ከበሬታ እንደነበራቸው በዘርፉ የተሰማሩ መምህራን ይናገራሉ።
ላለፉት 30 ዓመታት በመምህርነት ሙያ የዘለቁት መልሳቸው መንግሥቱ ቀደም ሲል መምህራን በየትኛውም አካባቢ ስንቀሳቀስ መምህርን የሚያውቅ በየትኛውም የዕድሜ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሰው ሁሉ ቅድሚያ ይሰጠን ነበር ነው ያሉት።
የማኀበራዊ አገልግሎት በሚሰጡባቸው ቦታዎች ጎራ ሲሉ ሰዎች ከተቀመጡበት ወንበር ተነስተው፣ ባርኔጣቸውን አውርደው፣ በክብር ያስተናግዷቸው እንደነበር አውስተዋል።
ተማሪዎችም ለመምህራን የነበራቸው ከበሬታ ልዩ እንደነበር ያስታወሱት መምህር መልሳቸው “አሁን ያን የመሰለ ውብ ግብረ ገብ ማን ወሰደብን?” ሲሉ በመቆጨት ይጠይቃሉ።
አንድ ቤተሰብ ልጁ በመምህር ከታጨች ደስታው ከቤተሰቡ ባለፈ ለአካባቢው ማኀበረሰብ ይጋባ ነበር የሚሉት መምህር መልሳቸው ልጁን ለመምህር ለመዳር እና ለመኳል የሚጥረው ወላጅም ጥቂት እንዳልነበር በትዝታ ወደ ኋላ ተመልሰው አጫውተውናል።
ይህም ማኀበረሰቡ ለሙያው የነበረውን ክብር ያሳያል ነው ያሉት።
መምህር የምታገባ ልጅም በሰርጓ ዕለት እንዲሲሉ ያሞካሿት ነበር፦
” የእኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ፣
አገባሽ አስተማሪ፤
ወሰደሽ አስተማሪ።”
ይባል ነበር።
መምህሩ “እኔ ዓለምን ዘዋሪ የኾነችውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንትንም ቢኾን አላደንቅም፤ ጠፈር ላይ የወጡትንም አላደንቅም፡፡ የማደንቀው እነዚህን ሰዎች ለትልቅ ደረጃ ያደረሷቸውን መምህራን ነው፡›› ተብሎ ተጽፎ ማንበባቸውን ነግረውናል። ይህም የዓለም ማኀበረሰብ ለመምህር ያለውን በጎ እሳቤ ያመላክታል ነው ያሉት።
መምህሩም ሰብዕናውን የጠበቀ፣ አንባቢ፣ የማኀበረሰቡን ወግ እና ባሕል ፍጹም አክባሪ እንደ ነበር ተናግረዋል።
ይህ ትውልድም እየተሸረሸረ የመጣውን ሙያተኛን የማክበር እሴት ቢመልሰው ያተርፍበታል ነው ያሉት።
ሌላዋ አስተያዬት ሰጭ መምህርት ሙሉ ባለው መምህራን የሀገር ምሰሶዎች፣ መምህርነት ደግሞ የሙያዎች አባት፤ መምህር የዕውቀት ብርሃን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ያለ መምህር የተማረ ትውልድ አይፈጠርም ያሉት መምህርቷ መምህር ከቀድሞ ጀምሮ ለሙያው ክብር ሰጥቶ እንደ ሻማ እየቀለጠ ይገኛልም ብለዋል።
ድሮ እና ዘንድሮን ያነጻጸሩት መምህርቷ ቀደም ሲል ከሱቅ ዕቃ ገዝተው መንገድ እንደጀመሩ ወጣቶች ተሽቀዳድመው ይይዙላቸው ነበር። ማኀበረሰቡ ለሙያው የሚሰጠው ላቅ ያለ ክብር ነበር አሉን።
ትንሹ ትልቁ፤ ሴት ወንዱ “እትዬ!” “ጋሽዬ” በሚል የክብር ስም መምህራንን ይጠራቸው እንደነበርም ጠቁመዋል።
አሁን ግን መተጋገዙ ቢቀር እንኳ ትልቅ ትንሽን እንዲኹም የትኛውንም ሙያተኛ ሲከበር ባለማየታቸው ቁጭታቸው ከፍተኛ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
መምህራን ትውልድን በዕውቀት፣ በአመለካከት እና በክህሎት በማዳበር ለሀገር ሰላም እና ዕድገት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። ትምህርት ደግሞ የሰውን ልጅ ክፉ አድርጎ አይቀርጽምና ኀብረተሰቡ “ክብር ለመምህራን እና ክብር ለትምህርት” ሊሰጥ ይገባዋልም ነው ያሉት።
መምህርቷ በየጊዜው ለተማሪዎቻቸው ስለመከባበር እሴት በማስተማር የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ መኾናቸውን ገልጸው ወላጆች እና አሳዳጊዎችም ልጆቻቸው ክብር ለሚገባው ክብር እንዲሰጡ መምከር እና መገሰጽ አለባቸው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ አመራር የልህቀት አካዳሚ ኘሬዝዳት ዛዲግ አብርሃ በአካዳሚው ይፋዊ ገጽ ላይ https://www.facebook.com መምህራን ለፕሬዝዳንቶች፣ ለኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች፣ ለፈጠራ ባለቤቶች እና ሀገርን ለሚቀይሩ ሰዎች መሠረት ናቸው ሲሉ አስፍረዋል።
መምህራን የተማሪዎች ቀራጮች ብቻ ሳይኾኑ የሀገራት “አርክቴክቶችም” ጭምር ናቸው ሲሉ ጽፈዋል።
እያንዳንዱ ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የፈጠራ ባለቤት ወይም አብዮተኛ በጊዜው ከመምህር ፊት ለፊት ተቀምጦ ተምሯል። ስለዚህ መምህራንን ማክበር ማለት የሥልጣኔን እውነተኛ “አልኬሚስቶች”ን ማክበር ማለት ነው ባይ ናቸው። ያለ መምህር አንድ ሀገርም ኾነ ኀብረተሰብ ወዴትም ሊደርስ አይችልም በማለትም አትተዋል።
አቶ ዛዲግ መምህራን የሃሳብ ሠራዊት፣ የሥልጣኔ ወታደሮች ናቸው ብለዋል።
ደቡብ ኮሪያ እና ሲንጋፖር በመምህራን ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ በአንድ ትውልድ ውስጥ ሀገራቸውን ከድህነት ወደ ሃብት ማማ ማሻገር ችለዋልም ሲሉ አብነት አስቀምጠዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር ፕሬዝደንት ዮሐንስ በንቲ ማኀበሩ ከ700 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ተናግረዋል።
ማኀበሩ ሙያው ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ ሠርቷል፤ እየሠራም ይገኛል ያሉት ዶክተር ዮሐንስ መምህራን በየጊዜው የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል።
ሙያው ሳቢ እንዲኾን እና በርካታ ወጣቶች መምህርነትን መርጠው የሚማሩት ሙያ እንዲኾን ማኀበሩ እየሠራ ነውም ብለዋል።
መምህራን ትውልድ ይገነባሉ ያሉት ዶክተር ዮሐንስ የመምህራን የማስተማር (የአካዳሚክ) ነጻነት እንዲከበር እየተሠራ ነው። መምህራንም ጥበቃ (ከለላ) እንዲደረግላቸው ማኀበሩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
ክብር ለመምህራን!
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleዳኞች ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል።
Next article“የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 8 በመቶ አድጓል” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ