ዳኞች ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል።

3
ባሕር ዳር: መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ጉባኤ መካሄድ ከጀመረበት ከመስከረም 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ ዳኞች ምክንያታዊ ውሳኔ መስጠት እንዲችሉ የሚያግዙ ሥልጠናዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው።
በጉባኤው የክልሉ ዳኞች ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከሉ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እና ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ ለሚያጋጥሟቸው ጉዳዮች በምክንያታዊነት ውሳኔ መስጠት እንዲችሉ የሚያግዛቸውን ሥልጠና ተከታትለዋል።
ኢትዮጵያ እና ፍልሰት፣ የሕግ እና የአደረጃጀት ማዕቀፎች፣ ወንጀልን መከላከል እና መቆጣጠር እንዲኹም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የዳኝነት አካላት ሚና በሚል ይዘት የግንዛቤ ፈጠራ ሥልጠናው ተሰጥቷል።
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የዳኞችን ሚና በሚመለከት የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ሴክሬታሪያት ኀላፊ አብርሃም አያሌው ናቸው።
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ውስብስብ፣ ተለዋዋጭ፣ ድንበር ተሻጋሪ፣ በተደራጁ ግለሰቦች እና መረቦች የሚፈጸም፣ የረቀቀ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም እና ከፍተኛ ገንዘብ የሚዘዋወርበት መኾኑ በሥልጠናው ተነስቷል።
ድርጊቱን በመከላከሉ ረገድ ዳኞችን ጨምሮ መላው ኅብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ተጠይቋል።
የአማራ ክልል ካለው አቀማመጥ የተነሳ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ፣ መተላለፊያ እና መዳረሻ ከኾኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ መኾኑ ተነስቷል። ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል ዳኞች የወንጀል ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመበየን እና በመተርጎም፣ ተጎጅዎችን ማዕከል ያደረገ ፍትሕ በማስፈን፣ ድንበር ዘለል የዳኝነት አካላት ትብብርን በማጠናከር እና ከወንጀሉ ጋር የተገናኘ ንብረትን በማገድ እና በመያዝ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ በቀረበው ገለጻ ተጠይቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለመቀየር ኢትዮጵያውያን እጅ እና ጓንት ኾነው በጋራ መጓዝ ይገባቸዋል።
Next articleመምህራን ትውልድ ቀራጮች ብቻ ሳይኾኑ የሀገር “አርክቴክቶችም” ናቸው።