የተሻለ የትምህርት ጥራት ለማምጣት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት መገንባት ያሥፈልጋል።

1
ሰቆጣ ፡መስከረም 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሰሜኑ ጦርነት በማውደማቸው እና በደረጃ ማነስ ምክንያት 16 ትምህርት ቤቶች በዳስ እና በዛፍ ጥላ ስር ያስተምራሉ።
እነዚህን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
በዝቋላ ወረዳ አዳነ ሲግ ቀበሌ ቅዳሚት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዓለም አቀፍ የሕጻናት አድን ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ በ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር
ባለ አራት ክፍል አንድ ሕንጻ ተገንብቶ ተመርቋል።
ትምህርት ቤታቸው ዘመናዊ ኾኖ መሠራቱ ለመማር ያላቸውን ፍላጎት እንዲጨምር እና ውጤታማ እንዲኾኑ እንደሚያግዛቸው ተማሪ ኮለ ተክላት እና ተማሪ ሰላም ዳዊት ተናግረዋል።
የዝቋላ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የጸዳው ገላው የባለፈውን ዓመት ጨምሮ ድርጅቱ በዝቋላ ወረዳ 12 የመማሪያ ክፍሎችን ከነሙሉ ግብዓታቸው አሟልቶ ማስረከቡን ገልጸዋል።
ይህም ከ600 በላይ የሚኾኑ ተማሪዎችን ከዛፍ ጥላ ወደ ክላስ መቀየር የቻለ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሹመት ጥላሁን ዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት በትምህርቱ ዘርፍ እየሠራ ያለው ተግባር አበረታች ነው ብለዋል።
በዋግ ኽምራ የተሻለ የትምህርት ጥራት ለማምጣት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት መገንባት ያሥፈልጋል ያሉት አቶ ሹመት በቀጣይም ይህንን ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ተቋማዊ ሪፎርሙ ወቅታዊ ችግርን ተሻግሮ መጻዒውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleበአማራ ክልል የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት በዘመቻ ሊሰጥ ነው።