ሉሲ ሜዲካል ቢዝነስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በተለያዩ ዘርፎች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።

3
ደሴ: መስከረም 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሉሲ ሜዲካል ቢዝነስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በተለያዩ ዘርፎች በዲፕሎማ ያሠለጠናቸውን ከ360 በላይ ተማሪዎች አስመርቋል።
በ2015 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራ የጀመረው ሉሲ ሜዲካል ቢዝነስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ 572 ተማሪዎችን ተቀብሎ በዲፕሎማ መርሐ ግብር እና በአራት የትምህርት ክፍሎች ሲያስተምር ቆይቷል።
ኮሌጁ አሁን ላይ በዲፕሎማ በስድስት ትምህርት ክፍል በዲግሪ ደግሞ በአምስት የትምህርት ክፍሎች ሥልጠና ይሰጣል።
በዛሬው ዕለትም በተለያዩ ዘርፎች ሲያሠለጥናቸው የነበሩ 365 ተማሪዎችን አስመርቋል። ከዕለቱ ተመራቂዎች መካከል 244 ያህሉ ሴቶች ናቸው።
ኮሌጁ በ2016 ዓ.ም ከ360 በላይ ሠልጣኞችን ተቀብሎ በዲግሪ መርሐ ግብር እያሠለጠነ ሲኾን አሁን ላይ በጠቅላላ ከ800 በላይ ሠልጣኞችን በማሠልጠን ላይ መኾኑን የኾሌጁ ፕዝዳንት ተመስገን ታመነ ተናግረዋል።
የሀገራችንን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት የሚሠራው ኮሌጁ በፋርማሲ፣ በነርሲንግ እና ሜዲካል ላበራቶሪ ሠልጥነው የተመረቁ ሠልጣኞች መኾናቸውን ገልጸዋል።
በቆይታቸው ለሀገር እድገት አስተዋጽኦ ያላቸው ኾነው እንዲወጡ በትኩረት መሠራቱንም ተናግረዋል። ለትምህርት ጥራት መረጋገጥም የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
ተመራቂዎች በሚሠማሩበት የሥራ ዘርፍ የለውጥ እና የእድገት ተምሳሌት በመኾን መሥራት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ማለትም አካውንቲንግ እና ፋይናንስ፣ በሰው ሃብት ልማት እንዲሁም በዳታ ቤዝ አሥተዳደር ሠልጣኞችን ተቀብሎ ያሰለጥናል ነው ያሉት።
ኮሌጁ የማኅበረሰብ አገልግሎትን እንደ መርሕ በመያዝ አቅም ለሌላቸው 12 ተማሪዎች የነጻ የትምህርት ዕድል በመስጠት እያስተማረ መኾኑንም አቶ ተመስገን ገልጸዋል።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ከ80 በላይ ለሚኾኑ አቅመ ደካሞች የጤና መድህን ክፍያ በመክፈል ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑንም አንሰተዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኮሌጁ ቦርድ ሰብሳቢ ይመር አያሌው (ዶ.ር) የኮሌጁ የመጀመሪያ ተመራቂ በመኾናቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ተመራቂዎች ሕዝባችሁን እና ሀገራችሁን በእውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ማገልገል እንዳለባቸውም ቦርድ ሰብሳቢው ይመር አያሌው(ዶ.ር) አሳስበዋል።
የደሴ ከተማ ሥራ እና ስልጠና መምሪያ ኀላፊ አብዱልሐሚድ ይመር ትምህርት የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ቁልፍ መኾኑን አንስተዋል። ትምህርትን ለማሳለጥ የሰላም ሚና ከፍተኛ ስለመኾኑ ገልጸዋል። ሰላምን መጠበቅ የነሱም ኀላፊነት መኾኑንም ለተማሪዎች ተናግረዋል።
የዕለቱ ተመራቂዎችም በሚሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ኅብረተሰቡን በቅንነት እና በተማኝነት በማገልገል ሙያዊ ኀላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
በሠለጠኑበት ዘርፍ ብቻ ሥራ ከመጠበቅ አስተሳሰብ ወጥተው በራሳቸው ሥራ በመፍጠር ለሌሎች ወገኖች አለኝታ ለመኾን እንደሚጥሩም አንስተዋል።
ሉሲ ሜዲካል ቢዝነስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዙር ተመራቂዎቹን ባስመረቀበት ወቅት ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ አራት ተማሪዎች ዲግሪያቸውን በነጻ የሚማሩበትን ዕድልም አመቻችቷል።
ዘጋቢ:- አሊ ይመር
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለብዙ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥ ፕሮጀክት በደብረ ብርሃን ከተማ ሊገነባ ነው።
Next article“ፖሊስ ልቡ፣ አስተሳሰቡ እና እጁ ከጽንፈኝነት፣ ጎጠኝነት እና ሌብነት የፀዳ መኾን ይኖርበታል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ