ለብዙ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥ ፕሮጀክት በደብረ ብርሃን ከተማ ሊገነባ ነው።

3
ደብረ ብርሃን: መስከረም 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኮሜዲያን እሸቱ መለሰ አማካኝነት የተቋቋመው “ለመጽደቅ የዘለቄታ” የተሰኘ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት በደብረ ብርሃን ከተማ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለማስገንባት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል።
ፕሮጀክቱ የአዳሪ ትምህርት ቤት፣ ፊዚኦ ቴራፒ ትምህርት ቤት፣ የተለያዩ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች፣ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች፣ የኮሜዲያን ተሰጥኦ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤት፣ ለሴቶች እና እናቶች የቢዝነስ ሥራ ማሠልጠኛ የሥራ ማዕከል ፕሮጀክቶችን በአካባቢዉ ላይ ያከናውናል ተብሏል።
በስድስት ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባው ፕሮጀክቱ በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በእምዬ ምኒልክ ክፍለ ከተማ ሎሬት አፈ ወርቅ ተክሌ ቀበሌ ሥር በሚገኘው ጋንጎና ቦራሌ ንዑሥ ቀበሌዎች ላይ እንደሚገነባ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ ማኅበረሰቡ ለሚያነሳቸው የረጅም ጊዜ ጥያቄዎችን የሚመልስ ነው ያሉት የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ናቸው። ለብዙ ችግሮች መፍትሔ የሚኾን እንደኾነም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በሕዝብ ተሳትፎ የሚገነባ በመኾኑ ለሀገራችን ምሳሌ የሚኾን ነው ብለዋል። ተገንብቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከተማ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
በጤና ዕክል የመንቀሳቀስ ችግር ያለባቸው ልጆችን የሚንከባከቡ እናቶች፣ የፊዚዮ ቴራፒ ሥልጠና የሚያገኙበት እና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ማዕከል እንደሚኖረው የፕሮጀክቱ ሥራ አሥኪያጅ ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ዕውን እንዲኾን የአካባቢው ማኅበረሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ፕሮጀክቱም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ብርቱካን ማሞ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ተቋማዊ ሪፎርሙ የክልሉ ፖሊስ የተደራጁ ወንጀሎችን እና የፀረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በቀላሉ ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው” ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር)
Next articleሉሲ ሜዲካል ቢዝነስ እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በተለያዩ ዘርፎች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።