
ባሕር ዳር ፡መስከረም 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ትልቁ የግዕዝ እና የአማርኛ መዝገበ ቃላት የኾነው “መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” የተሰኘው ታላቅ ሥራ የተጠናቀቀው በሦስት ሊቃውንት ትውልድ ቅብብሎሽ ነው።
መጀመሪያ በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የተወጠነው ይህ ሥራ ሊቁ በ1908 ዓ.ም ሲያርፉ ለደቀ መዝሙራቸው ለአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በአደራ ተላለፈ።
“የቃላት ጉልላት” በመባል የሚታወቁት አለቃ ኪዳነ ወልድ ከአስተማሪያቸው የተረከቡትን ሥራ ለ16 ዓመታት ከቀጠሉ በኋላ በጤና እክል ምክንያት በ1936 ዓ.ም ሲያርፉ የማጠናቀቁን ኀላፊነት ለደቀ መዝሙራቸው ለአለቃ ደስታ ተክለወልድ አሳልፈው ሰጡ።
አለቃ ደስታም የመምህራቸውን ህልም እውን ለማድረግ ለ12 ዓመታት በትጋት ከሠሩ በኋላ መዝገበ ቃላቱን በ1948 ዓ.ም አሳትመው ለትውልድ አበቁት።
አለቃ ደስታ ተክለወልድ ከዚህም በተጨማሪ በንጉሥ ተፈሪ መኮነን ትዕዛዝ እና በአለቃ ኪዳነ ወልድ መሪነት “አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት” የተሰኘውን ሌላ ታላቅ ሥራ የሠሩ ሲኾን ይህም ሥራ ያለ ረዳት በብቸኝነት በ30 ዓመታት ውስጥ ተዘጋጅቶ በ1962 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ታትሟል።
በቋንቋው ሕግጋት ላይ ያላቸውን ጽናት ለማሳየትም የተለመደውን የፊደል ቅደም ተከተል በመተው የመዝገበ ቃላቱን አደረጃጀት በ “አበገደ” ተራ መሠረት አድርገውታል።
አለቃ ደስታ ለኢትዮጵያ ቋንቋ ዕድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ አድርጓቸው እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ምንጭ፦ ብላክ ላየን መጽሐፍ

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በ1948 ዓ.ም (እንደ አውሮፓውያን ዘመን በ1955) በዚህ ሳምንት ነበር የተመሠረተው። “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የባሕር ኃይል” በመባልም ይታወቅ ነበር።
ዋና የመሠረቱ እና የሥልጠና ማዕከሉ የነበረው ምጽዋ ላይ የነበረ ሲኾን በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን 3 ሺህ 500 ሠራተኞች እና 26 መርከቦች ነበሩት።
በወቅቱ 1ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የቀይ ባሕር ጠረፍ እንደነበረውም ይነገራል።
ወታደሮቹ በዓለማችን ታዋቂ ከኾኑ የባሕር ኃይሎች (በኖርዌይ፣ በብሪታንያ፣ በአሜሪካ እና በኢጣሊያ) የሠለጠኑ ሲኾኑ በአስመራም የራሱ የባሕር ኃይል ኮሌጅ የነበረው ነው።
ንጉሡ ከወረዱ በኋላ ባሕር ኃይሉ የሶቭየት ኅብረትን ሞዴል ተከትሎ በዋናነት በሶቪየት ስሪት መርከቦች የታጠቀ ነበር። ነገር ግን 1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ሲከሰት መርከቦቹ ወደ ጅቡቲ እና የመን መሰደዳቸውን እና በኋላም መሸጣቸውን ታሪክ ይነግረናል።
ዛሬ ላይ ከጠቅላላው ኃይል የተረፈችው ብቸኛዋ መርከብ ‘ጊቢ’ የተባለችው ስትኾን የቅኝት ጀልባም ናት። አዲስ ዘመን ጋዜጣ በየካቲት 2011 ዓ.ም ባወጣው ዕትሙ ላይ ይህችው የሀገር ምልክት እና ታሪክ ነጋሪ የቀይ ባሕር የቅኝት ጀልባ ጣና ውስጥ እንዳለች ገልጿል።
በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የብሔራዊ ጥቅምን እና ደኅንነትን ለማስጠበቅ በአዋጅ ቁጥር 1100/2011 መሠረት የባሕር ኃይሏን ዳግም አቋቁማለች።
አዲስ የተመሠረተው ኃይል ለንግድ መርከቦች ጥበቃ እና ለቀጣናዊ ሚዛን አስፈላጊ በመኾኑ እየተደራጀ እና እየተጠናከረም ነው። ይህ ትውልድ ትልቅ ታሪካዊ ኃላፊነት ወድቆበታል።
ኢትዮጵያ በግፍ እና በሴራ ያጣችውን የባሕር በር በዓለማቀፍ ሕግ መመለስ ይገባዋል። ይህም የሚኾነው ሕዝቡ አንድ ኾኖ ጉዳዩን ዓለማቀፍ አጀንዳ ማድረግ ሲችል ነው።
እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ ሕዝብ ይህን ጉዳይ ጫፍ ማድረስ እና ሀገሪቱን ወደ ነበረችበት ማማ መስቀል ከሁሉም ይጠበቃል።
ምንጭ፦ ብላክ ላየን መጽሐፍ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ እና የተለያዩ ጽረ ገጾች።

በየዓመቱ ጥቅምት 5 (በኢትዮጵያውያን መስከረም 25) የሚከበረው ይህ ቀን መምህራን ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማስታወስ እና የሚገባቸውን ክብር ለመስጠት ዓላማ ያደረገ ነው።
ይህ ቀን የተመሠረተው እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ጥቅምት 5/1966 የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (UNESCO) እና ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (ILO) በፓሪስ ውስጥ መምህራንን ስለሚመለከት የውሳኔ ሃሳብ ባሰፈሩት ሰነድ ላይ ተመስርቶ ነው።
ይህ ሰነድ ለመምህራን መብት እና ኀላፊነት ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ያስቀመጠ ነው።
ይህንን ታሪካዊ ክስተት ለማሰብ UNESCO እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን በ1994 ጥቅምት 5 ዓለም አቀፍ የመምህራን ቀን እንዲኾን በይፋ አውጇል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቀኑ ለመምህራን ያለውን ክብር ለመግለጽ እና ሙያውን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ለመዳሰስ በዓመት አንድ ጊዜ ይከበራል።
የዚህ ዓመት የመምህራን ቀንም “መምህርነትን እንደ ትብብር ሙያ መቅረጽ” በሚል ጭብጥ ይከበራል።
መምህራንን ማክበር ብቻ ሳይኾን የሚወዱትን ሙያ የተሻለ ትውልድ እንዲቀርጹበት ለማድረግ ያለባቸውን ችግሮች መፍታትም ከሁሉም ይጠበቃል።
ምንጭ፦ ዩኔስኮ ድረ ገጽ
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!