“የኮሪደር ልማት እና አጠቃቀማችን”

2
ባሕር ዳር፡ መስከረም 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከተሞች የምጣኔ ሃብት እና የፖለቲካ ማዕከል ናቸው። የዕውቀት እና የሥልጣኔ ምንጭነታቸውም እንዲሁ።
ከተሞች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ጽዱ፣ውብ፣ ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እና ጎብኝዎችን የሚስቡ ኾነው እየተሠሩ ነው።
”የኮሪደር ልማት” ባሕር ዳርን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች ተሠርቶ እየተጠናቀቀ እና ባልተጀመረባቸው ከተሞች ደግሞ እየተጀመረ ነው። ጀምረው ያጠናቀቁትም ሁለተኛ ዙር እየቀጠሉ ነው።
ከእነዚህ የኮሪደር ልማት ተጠቃሚ ከተሞች ውስጥ የባሕር ዳር ከተማ ተጠቃሽ ናት። ከተማዋ ጣናን የመሰለ ሰፊ እና ሕይወት የሚዘራ ሐይቋ፣ ሜዳማነቷ እና ዘንባባዎቿ ላይ የኮሪደር ልማት ሲጨመር የበለጠ ውብ አድርጓታል።
የመኪና፣ የብስክሌት እና የእግረኛ መንገድ ተለያይቶ የተሠራባቸው መንገዶቿ፣ አረንጓዴ የተሸፈኑ መስመሮች፣ የጣና ነፋሻ አየር የሚገባበት ሰፊ መተላለፊያ፣ ለመብራት እና ለደኅንነት አገልግሎት የሚውሉ መሣሪያዎች ተጨማምረው ከተማዋን ደስታ የምታላብስ አድርጓታል። ጌጠኛ መብራቶቿ እና መዳረሻ ጎዳናዎቿ ውበቷን የሚያላብሷት ኾነዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎችም ኾኑ እንግዶች በጣና ዳርቻዎች እንዲዝናኑ እና የሥራ ዕድል እንዲያገኙ፣ መንገዶች ውብ እና ምቹ ኾነው ከአደጋ ነጻ እንዲኾኑ ማድረጉ የልማቱ ገጸ በረከቶች ናቸው።
አንደኛው ዙር ግንባታ ተጠናቅቆ ወደ ሁለተኛው ዙር የተገባበት የኮሪደር ልማት እንደታሰበው ሊያገለግል እና ለሌሎችም አርዓያ ይኾን ዘንድ ታዲያ የተጠቃሚውንም ቀና አስተሳሰብ እና አጠቃቀም ይጠይቃል።
ከእግረኛ መንገድ ወጥቶ በመኪና እና በብስክሌት መንገድ መጓዝ፣ ብስክሌትን በእግረኛ መንገድ መጋለብ፣ የጌጥ እጽዋቶችን ማበላሸት፣ ወዘተ ገና ከጅምሩ የሚስተዋሉ ችግሮች እንደኾኑ መታዘብ ይቻላል።
ደንብ አስከባሪዎች እና የትራፊክ ፖሊሶች የመንገድ አጠቃቀሙን ለማለማመድ ሲሞክሩ እየታዩ መኾኑ የሚበረታታ ነው።
ሕንጻዎች ተመሳሳይ ቀለም ተቀብተው ለእንግዶች ሳቢ እየተደረገ ነው።
ዲጂታላይዜሽንን በመተግበር ፈጣን፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት፣ ወንጀልን በመከላከል ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማስፈን የተጀመረው ሥራም ተስፋ ሰጭ ነው።
ይህ ጅምር የከተሞች ልማት ሊሰፋ እና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው። የአንድ ሰሞን ሥራ እንዳይኾን የኅብረተሰቡ ስጋትም ሊቀረፍ ይገባዋል።
ከተሞች ጽዱ ኾነው በየኮሪደሩ አፍንጫ እያስያዘ የሚያስመርረው ሽታ ይቀር ዘንድ የኮሪደር ልማቱ አካል ኾኖ ሊተገበር ይገባዋል።
ለውጥ ከአነስተኛ ነገሮች እና ከራስ ይጀምራል እና የከተሞችን መለወጥ፣ ንጹህ እና ጽዱ መኾን የሚፈልግ ሁሉ ሥራውን ለመንግሥት ብቻ መተው የለበትም።
የከተማ ልማት ዓላማ እንዲሳካ እና እንድንጠቀም እያንዳንዳችን በየዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያችን ተባባሪ መኾንም ይጠበቅብናል።
የከተማ እንቅስቃሴው ሕግን ያከበረ፣ ለደኅንነት እና ለጽዳት ምቹ እንዲኾን በደንብ አስከባሪዎች እና ፖሊሶች ሲታዘዙ ከመተባበር ይልቅ ለመተቸት የሚዳዳቸው ሰዎችም ይስተዋላሉ።
በየዕለቱ ቆሻሻን በማጽዳት እና የማያቆሽሽ ነዋሪ መፍጠር ያስፈልጋል። በየቦታው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫቶች እና መጸዳጃ ቤቶች ሊዘጋጁ ይገባል። ኅብረተሰቡም እስኪለምደው ድረስ ደንብ አስከባሪዎች እና በጎ ፈቃደኞች ጠንክረው ሊሠሩበት ይገባል።
ከተማዋን ለማዘመን የተጀመሩ ሥራዎችም ዘላቂ እንዲሆኑ የኅብረተሰቡ ባለቤትነት ያስፈልጋል። ሲጠናቀቁም ለየአካባቢው ማኅበረሰብ ማስረከብ፤ በጽዳት እና ጥበቃው ላይም የውድድር ስሜት መፍጠር ለአጠቃቀሙ ጤናማነት እና ለዘላቂነቱ አስተዋጽኦ ማበርከት ተገቢ ነው።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከ200 በላይ ተማሪዎችን ከዳስ ወደ ክላስ የሚመልስ ትምህርት ቤት ተመረቀ።
Next articleየሦስት ሊቃውንት የአሻራ ቅብብሎሽ