
ሰቆጣ፡ መስከረም፡ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ዙርያ ወረዳ በዓለም አቀፍ የሕጻናት አድን ድርጅት የበጀት ድጋፍ የተገነባ ትምህርት ቤት ተመርቋል።
ከዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት በተገኘ የበጀት ድጋፍ በቲያ ቀበሌ ቲያ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለ አራት ክፍል ሕንጻ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ተማሪ አለምነው አበበ በቲያ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። የትምህርት ቤቱ መገንባት ለመማር ያለውን ፍላጎት ከፍ እንዲል እንዳገዘው ገልጿል።
ባለፉት ዓመታት በዳስ እና በዛፍ ጥላ ሥር መማሩ በውጤቱ ላይ ተጽዕኖ ያሳድርበት እንደነበርም አሥታውሷል።
የዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት በቲያ ቀበሌ ዘመናዊ ትምህርት ቤት በመገንባቱ ምሥጋና ያቀረቡት ደግሞ የቀበሌው ነዋሪ አቶ ስንታየሁ ወርቁ ናቸው።
የቀበሌው ሕዝብም አጥር በመሥራት እና የተገነቡ ግንባታዎችን በመጠበቅ በኩል የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል።
በቲያ ቀበሌ የተገነባው ትምህርት ቤት ከ200 በላይ የሚኾኑ ተማሪዎችን ከዳስ ወደ ክላስ የመለሰ ትልቅ ፕሮጀክት መኾኑን የሰቆጣ ዙርያ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበባው መንግሥቴ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት በወረዳው በጤና፣ በትምህርት እና በግብርና ዘርፍ በርካታ ድጋፎችን ማድረጉን ያሥታወሱት ኀላፊው በቀጣይም የዋግ ኽምራን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ በዳስ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ወደ ክላስ ለመቀየር አጋዥ ድርጅቶች እንዲያግዙም ጠይቀዋል።
በዓለም አቀፍ የሕጻናት አድን ድርጅት የስፖንሰርሺፕ ፕሮግራም የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ኢንጅነር ሰሎሞን መልአከብርሃን በቲያ ቀበሌ የተገነባው ሕንጻ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት ሲኾን በውስጡም አራት የመማሪያ ክፍሎችን ከእነወንበራቸው ያሟሉ ናቸው ብለዋል።
በትምህርት ቤቶች ላይ ድጋፍ ማድረግ በነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናት ላይ እንደመሥራት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በቀጣይም መሠል ድጋፎችን በማፈላለግ እንደሚደግፉም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!