
ጎንደር፡ መስከረም ፡ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዳሸን ቢራ ፋብሪካ ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ውጭ የወጣባቸውን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
ፋብሪካው ድጋፍ ያደረገው በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲማሩ ለመርዳት እንደኾነ የጎንደር ዳሸን ቢራ ፋብሪካ የማኅበረሰብ ዘርፍ መምሪያ ኀላፊ እንዳልካቸው አበበ ተናግረዋል።
ፋብሪካው 60 ሺህ ደብተሮችን እና 30 ሺህ እስክሪፕቶዎችን ድጋፍ ያደረገ ሲኾን በአጠቃላይ 5 ሚሊዮን 400 ሺህ ብር በላይ ወጭ እንደተደረገባቸውም አስረድተዋል።
ዳሸን ቢራ ፋብሪካ ተማሪዎችን በትምህርት ቁሳቁስ ለመደገፍ ካደረገው ጥረት ባሸገር በትምህርት ዘርፉ የሚታዩ የክፍል ጥበትን ለመቅረፍ እና አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ተቋማዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳደር፣ በምዕራብ እና ሰሜን ጎንደር ዞን አሥተዳደር ሥር የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ድጋፍ የተደረገላቸው ናቸው።
የተደረገው ድጋፍ ወቅቱን የጠበቀ እና በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ትምህርታቸውን መከታተል የማይችሉ ተማሪዎችን ችግር የሚያቃልል መኾኑን በድጋፍ ርክክብ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የጎንደር ከተማ ቀበሌ 19 ነዋሪ ወይዘሮ አስቴር አዱኛ ተናግረዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የወገራ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤትን ወክለው በርክክብ መርሐ ግብሩ የተገኙት አቶ ፈንታሁን ገበየሁ የተደረገው ድጋፍ የተሳካ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር የሚያችል መኾኑንም አብራርተዋል።
አስተያየት ሰጭዎቹ በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል የማይችሉ ተማሪዎችን ለመርዳት በሚደረገው ሂደት ልክ እንደ ዳሸን ፋብሪካ ሁሉ ሌሎች ድርጅቶችም የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፋብሪካው በጎንደር ከተማ ማራኪ ክፍለ ከተማ በ225 ሚሊዮን ብር የአዳሪ ትምህርት ቤት ለማስገንባት የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጡም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ኃይሉ ማሞ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!