
ባሕር ዳር፡ መስከረም፡ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የዳኞች ጉባኤ ቀጥሏል። “የጋራ ርዕይ ለጠንካራ የዳኝነት ሥርዓት” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ የሚገኘው ጉባኤው በዛሬው ውሎው በባሕል ፍርድ ቤቶች ላይ መክሯል።
በባሕላዊ ፍትሕ ላይ ጥናት ያቀረቡት በኢኒስቲትዩት ፎር ሴኩሪቲ ስተዲስ ከፍተኛ ተማራማሪ ታደሰ ስሜ (ዶ.ር) ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ፍትሕ ለተነፈጉ ወገኖች ፍትሕ እየሰጡ መኾናቸውን ገልጸዋል። ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች በየክልሎች እየተቋቋሙ ወደ ሥራ እየገቡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ነገር ግን ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች መሠልጠን እና መብቶችን በተሟላ መልኩ ማክበር ይገባቸዋል ነው ያሉት። ሕገ መንግሥቱ የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች እንዲቋቋሙ ዕውቅና እንደሰጣቸውም ተናግረዋል።
ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ሲቋቋሙ የተገፋውን ባሕል መመለስ እንደሚችሉም ተናግረዋል። የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ከተፈለገ ለባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ዕውቅና መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ውስጥ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓት እንዳለውም አንስተዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ጉዳዮች የሚፈቱት በባሕላዊ ፍርድ ቤቶች መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች እርቅን ዘላቂ ለማድረግ ሚናቸው የላቀ እንደኾነም ገልጸዋል።
የባሕላዊ የፍርድ አገልግሎቶች በየአካባቢው የሚገኙ በመኾናቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ ታማኝነት አላቸው ብለዋል። ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ቀላል እና ወጭ ቆጣቢ በመኾናቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ ተመራጭ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት።
በባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የሚፈጸሙ ሥነ ሥርዓቶች በሙሉ ሰብዓዊ መብቶችን የሚያከብሩ መኾን እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የሴቶችን መብት ማክበር እንደሚገባቸውም አመላክተዋል። በሽማግሌዎች መካከል ሴቶች መሳተፍ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ባሕላዊ ሥርዓቱ ተዓማኒ እንዲኾን ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ከተጽዕኖ መጠበቅ እና ነጻ እንዲኾኑ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅን ያቀረቡት የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሃናን አበበ መንግሥት ባሕሎችን የማሳደግ እና የመጠበቅ ኀላፊነት እንደተሰጠውም ተናግረዋል። ኀላፊነት እና ግዴታውን ለመወጣት የባሕል ፍርድ ቤቶችን ማቋቋሙንም ገልጸዋል።
ጉዳያቸው በባሕል ፍርድ ቤቶች እንዲታዩላቸው የሚፈልጉ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመኖራቸው ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ተደራሽ በመኾናቸው ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ሕግ መንግሥታዊ እና ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ መቀረጽ ስላለባቸው በአዋጅ መቋቋማቸውን ነው የተናገሩት።
የባሕል ሕግ እና እሴቶችንም ማስጠበቅ፣ ለባሕል እና እሴት ዕድገት አስተዋጽኦ ማበርከት ስላስፈለገ ፍርድ ቤቶቹ እንዲቋቋሙ ኾነዋል ነው ያሉት።
የባሕል ፍርድ ቤቶች ሲመሠረቱ መርሆዎች እንዳሏቸው የተናገሩት ወይዘሪት ሃናን በፈቃድ ላይ የተመሠረተ መኾን፤ ባሕላዊ ሥርዓትን ማስጠበቅ፣ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ መኾን እና የሰብዓዊ መብትን ማክበር መርሆዎቹ መኾናቸውን ገልጸዋል።
አድሎ አልባነት፣ የሴቶች እኩልነት፣ የሕጻናት ጥቅም እና ቅጣቶቹ ኢ-ሰብዓዊ እንዳይኾኑ ማድረግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
የባሕላዊ ፍርድ ቤት ሽማግሌዎች ሥነ ምግባር ያላቸው፣ አድሎ የሌለባቸው፣ በጥቅም የማይሠሩ፣ ምስጢር የሚጠብቁ፣ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተሳታፊ ያልኾኑ መኾን እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።
የባሕል ፍርድ ቤቶች በሕዝብ ግልጽ በኾነ ቦታ ላይ የሚካሄዱ መኾናቸውን ተናግረዋል። ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ዜጎች በእርቅ እንዲስማሙ፣ አብረው እንዲኖሩ እና ቂም እንዲሽር የማድረግ አቅማቸው ከፍ ያለ መኾናቸውንም አመላክተዋል።
የአዋጁን አፈጻጸም እንዲከታተል ለክልሉ ምክር ቤት ተጠሪ የኾነ እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠብሣቢነት የሚመራ የባሕል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት መቋቋሙንም ወይዘሪት ሃናን አንስተው ምክር ቤቱ የባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ሥራዎች እንደሚከታተልም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!