
ደሴ፡ መስከረም፡ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ስማይል ትሬን እና ፕሮጀክት ሐረር ከተባሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የፈገግታ ቀንን በማስመልከት በተፈጥሮ የላንቃ እና ከንፈር ክፍተት ላለባቸው በደሴ ከተማ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል በነጻ ሕክምና እየተሰጠ ነው።
በደሴ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል የፕሮግራሙ አስተባባሪ ዶክተር መሐመድ አብደላ በሆስፒታሉ በየሦሥት ወሩ ሕክምናውን በነፃ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ይህን ሕክምና ለማግኘት እስከ 50ሺህ ብር እንደሚጠይቅም ነው ያስረዱት።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የፕሮጀክት ሐረር አስተባባሪ ንጋቱ የሻምበል የክልሉ ጤና ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ባለፉት ስምንት ዓመታት በክልሉ ችግሩን ለማቃለል በየሩብ ዓመቱ ሕክምና እንዲሰጥ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
ሕክምናው በአማራ ክልል በደሴ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል እና በባሕር ዳር ጋምቢ የማስተማሪያ ሆስፒታል እንደሚሰጥ የተናገሩት አቶ ንጋቱ በደሴ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል ከመስከረም 23/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት ሕክምናው እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሕክምናውን ለ35 ሰዎች በነፃ ለመስጠት ነበር የታቀደው ያሉት አስተባባሪው እሰካሁን ከ50 በላይ ሰዎች ተመዝግበው ሕክምናው እየተሰጠ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
የከንፈር እና ላንቃ ክፍተት ሕመሙ የሚታየው ሕጻናት ሲወለዱ ነው ብለዋል።
ለሕመሙ አጋላጭ ምክንያት ከሚባሉት ውስጥ በዘር፣ በመጀመሪያዎቹ የእርግዝና ሦሥት ወራት ውስጥ የሲጋራ ማጨስ፣ የአልኮል መጠጥ፣ የጫት መቃም እንዲሁም በሐኪም ያልታዘዙ መድኃኒቶችን መውሰድ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ወንዶች ከሴቶች በበለጠ በዚህ ሕመም ተጠቂ መኾናቸውንም አሰተባባሪው አስረድተዋል።
የህመሙን ተጋላጭነት በተመለከተ በክልሉ የተሠራ ጥናት ባይኖርም በሀገር አቀፍ ደረጃ ግን ከ672 ሕጻናት አንዱ ተጠቂ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የተፈጥሮ የላንቃ እና ከንፈር ክፍተት የሚድን ሕመም በመኾኑ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግም ተገልጿል። በመጭው ጥቅምት ወር ሕክምናው በባሕርዳር ጋምቢ ሆስፒታል ይሰጣልም ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!