አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ ለማድረስ እየተሠራ ነው።

4

ባሕር ዳር፡ መስከረም፡ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ የወረቀት እና ህትመት ፋብሪካ ለ2018 የትምህርት ዘመን እያዘጋጀ ያለውን የመማሪያ መጽሐፍ አስጎብኝቷል።

የፋብሪካውን የመጽሐፍት ህትመት ሂደት የጎበኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምሀርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የመጽሐፍት ህትመት በትምህርት ሥርዓቱ መሟላት ካለባቸው ግብዓቶች መካከል አንዱ መኾኑን ገልጸዋል። ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉት መጽሐፍትም ስለተቀየሩ በየዓመቱ እየታተመ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

ትምህርት ቢሮው መጽሐፍትን በየዓመቱ በማሳተም ላይ መኾኑን የጠቀሱት ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መጻሕፍት ደግሞ ከፌዴራል መንግሥት ተረክበናል ብለዋል። አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ እንደሚደርስም ጠቅሰዋል።

በክልሉ የሚታተሙት መጽሐፍት ከቅድመ አንደኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉት ሲኾኑ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጽሐፍ እየታተመ ነው ብለዋል።

የሕዝብ ሃብት በኾነው ዓባይ የወረቀት ህትመት እና ፓኬጅንግ ፋብሪካ ህትመቱን እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ይህም በተፈለገው መልኩ ለማሳተም እና ክትትል ለማድረግ ምቹ እንደኾነ እና የውጭ ምንዛሪን ማስቀረቱን ገልጸዋል።

መጽሐፍቶቹን እስከ ዞን ድረስ እንደሚያደርሱ የተናገሩት ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ ኅብረተሰቡ ደግሞ እስከ ትምህርት ቤቶቹ እንደሚያደርስ ገልጸዋል። በራሱ ሃብት የታተመውን እና የልጆቹ መማሪያ የኾነውን መጽሐፍ ተንከባክቦ ለትምህርት ቤቶች እንዲያደርስም አደራ ብለዋል።

በትምህርት ዘመኑ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ተጨምሮበት የመጽሐፍት ሥርጭት አንድ ለአንድ ይደርሳል። መጽሐፍቶችም እስከ ዞን ድረስ እስከ ጥቅምት መጀመሪያ ይደርሳሉ ነው ያሉት። ወደየ ወረዳዎች እና ትምህርት ቤቶቹ ደግሞ የአካባቢው መሪዎች እና ኅብረተሰቡ ያደርሳሉ ብለዋል።

ዓባይ የወረቀት ህትመት እና ፓኬጅንግ ፋብሪካም ሥራዎቹ የበለጠ በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ እና ከክልሉ አልፎ ለሀገር የሚጠቅም እንዲኾን እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የዓባይ ወረቀት ህትመት እና ፓኬጂንግ ፋብሪካ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ታደሰ መላሽ ፋብሪካቸው በአማራ ልማት ማኅበር እና በአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ እንደተቋቋመ ጠቅሰው የትምህርት ዘርፉን የመደገፍ ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል።

ለ2018 የትምህርት ዘመንም 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን መጽሐፍት እያተመ መኾኑን ተናግረዋል።

ውጭ ይታተም የነበረውን መጽሐፍ በሀገር ውስጥ በማተም የውጭ ምንዛሬን መቆጠብ እንደተቻለም አስገንዝበዋል። ከውጭ እስኪጓጓዝ ይወስድ የነበረውን ጊዜም ማስቀረቱን ነው አቶ ታደሰ የጠቆሙት።

ፋብሪካው በሀገር ውስጥ የማይቻል ይመስል የነበረውን የህትመት ሥራም ሠርቶ ማሳየት መቻሉን አንስተዋል።

የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የከፍተኛ ግብር ከፋይነት እና የሚገኘውን ገቢ መልሶ ለሕዝቡ የልማት ሥራዎች ድጋፍ ማድረጉ የፋብሪካው ጠቀሜታዎች መኾናቸውን ዋና ሥራ አሥኪያጁ ጠቅሰዋል።

ለዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን ለመሸለም፣ የመማሪያ ቁሳቁስ ችግር ያለባቸውን ለመደገፍ እና ትምህርት ቤት ለመገንባት እየሠራ መኾኑ ፋብሪካው ለኅብረተሰቡ እየሰጠው ያለውን ጥቅም እንደሚያሳይ አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአረጋውያን በሚችሉት ነገር ሁሉ ለሀገራቸው አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው።
Next articleበተፈጥሮ የላንቃ እና ከንፈር ክፍተት ላለባቸው በደሴ ከተማ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል በነጻ ሕክምና እየተሰጠ ነው።