
ጎንደር: መስከረም 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ” የአረጋውያን ደህንነት እና መብቶችን በመጠበቅ ሁለንተናዊ ኀላፊነታችን እንወጣ” በሚል መሪ መልዕክት የአረጋውያንን ቀን አክብሯል።
ዕለቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሙሉቀን ጌታሁን ለሀገራቸው በተለያዩ መስኮች ያገለገሉ የሀገር ባለውለታ የኾኑ አረጋውያንን መብቶቻቸውን ማክበር እና ደህንነታቸውን መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዕለቱን ከማክበር ባሻገር አረጋውያንን ማገዝ እና መደገፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከ28 ሺህ 500 በላይ አረጋውያን መኖራቸውን የገለጹት ኀላፊዋ ከእነዚህም ውስጥ 94 አረጋውያን በክልሉ የገቢ ማስገኛ ሕንጻ በቀጥታ ድጋፍ የሚደረግላቸው ናቸው ብለዋል። 5 ሺህ 959 አረጋውያንን ደግሞ ቀጥታ የሴፍትኔት መርሐ ግብር ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አረጋውያንን በተቸገሩበት ነገር ሁሉ ለደገፉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ዕለቱን በማስመልከትም ሃብት በማሰባሰብ ለአረጋውያን ድጋፍ መደረጉን ያስታወሱት ኀላፊዋ የአልባሳት፣ የምግብ እና መሰል ድጋፎች መደረጉን አንስተዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተወካይ አወቀ ተፈራ በከተማ አሥተዳደሩ በምገባ ማዕከል 200 የሚደርሱ አረጋውያንን ለመመገብ የሚያስችል ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአረጋውያንን ቤት በመጠገን፣ በመመገብ እና ሌሎች በጎ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት።
የጎንደር ከተማ አረጋውያን ማኅበር ምክትል ሰብሳቢ
ዓለሙ አስማ እና የጎንደር ከተማ አረጋውያን ማኅበር ዋና ጸሐፊ ፍስሐ አዳነ ዕለቱ መከበሩ አረጋውያንን ለማገዝ ያስችላል ብለዋል።
አረጋውያን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የመኖሪያ ቤት የሌላቸውን ለማገዝ፣ በኢኮኖሚ ድጋፍ ለማድረግ እና የገቢ ማስገኛ መንገዶችን ለመፍጠር የበዓሉ መከበሩ ፋይዳ ያለው መኾኑን ተናግረዋል ።
“አረጋውያን በሚችሉት ነገር ሁሉ ለሀገራቸው አበርክቶ” እያደረጉ መኾኑንም አንስተዋል። ለአረጋውያን ክብር መስጠት ይገባልም ነው ያሉት ።
በዕለቱ ለአረጋውያን ድጋፍ ለሚያደርጉ በጎ አድራጎት ማኅበራት እና በጎ ፈቃደኞች ምስጋና እና እውቅና ተሰጥቷል ።
ዘጋቢ: ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!