
ባሕር ዳር: መስከረም 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅን እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ የማኅበረሰብ መር የተፋጠነ የውኃ ዝርጋታ እና ሃይጅን ፕሮጀክት (ዋሽ) በፊንላንድ እና በኢትዮጵያ መንግሥታት የሁለትዮሽ ትብብር እየተተገበረ የሚገኝ ፕሮግራም ነው።
ፕሮግራሙ በክልሉ 40 ወረዳዎች በዋናነት የገጠር መጠጥ ውኃ ተቋማት እና የመጻዳጃ ቤት ግንባታ፣ የአቅም ግንባታ እና የግብዓት አቅርቦት ተግባራት ላይ ትርጉም ያለው ሥራ እያከናወነ ይገኛል ያሉት የክልሉ ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ጥላሁን ሽመልስ ናቸው።
ፕሮጀክቱ በበጀት ዓመቱ ከ780 በላይ የውኃ ፕሮጀክቶችን እና መጸዳጃዎችን በመሥራት የገጠሩን የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።
የዋሽ ፕሮግራም በክልሉ የንጹሕ መጠጥ ውኃን በማሳደግ ጤንነቱ የተጠበቀ ማኅበረሰብ እንዲጎለብት በማድረግ በኩል ድርሻውን ሲወጣ የቆየ ፕሮግራም መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ
(ዶ.ር) ናቸው።
አርሶ አደሮች ፕሮግራሙን በመደገፍ በቀበሌ ደረጃ በገንዘብ፣ በጉልበት እና በቁሳቁስ በመደገፍ መንግሥት እና ረጅ ድርጅቶች ከሚያቀርቡት ሃብት ጋር በማዋሃድም ትልልቅ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
በቀጣይም ክልሉ ሊያደርግ ከሚፈልገው የገጠር የኮሪደር ልማት ማስፋፋት አኳያ አንዱ እና ዋናው የውኃ አቅርቦት በመኾኑ ይህንን ተግባር አጠናክረን መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
በመድረኩ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!