“ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ለውጤታማነት ቁልፉ ጉዳይ ነው” ስኬታማ ተማሪዎች

7

ደብረ ታቦር: መስከረም 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎችን ካሳለፉ ትምህርት ቤቶች መካከል በደብረ ታቦር ከተማ የሚገኘው ዳልሻ ቤዛዊት ዓለም ትምህርት ቤት አንዱ ነው።

መክሊት ወንድሙ እና ኢዩኤል አምላኩ ደግሞ ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል ናቸው። በዕቅድ ማንበባቸው እና በመምህራን የተደረገላቸው እገዛ ለዚህ ስኬት እንዳበቃቸው ተናግረዋል።

“ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ለውጤታማነት ቁልፉ ጉዳይ መኾኑንም” ያነሱት ተማሪዎቹ መምህራን የእረፍት ጊዜያቸውን መስዋዕት በማድረግ በተደጋጋሚ የሚሰጧቸው የሙከራ ፈተናዎችም ለውጤታቸው ጉልህ ድርሻ እንደነበረው ነው የተናገሩት።

የትምህርት ቤቱ የሥነ ሕይዎት ትምህርት መምህር ውዱ አያሌው ተማሪዎችን ለማብቃት እና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሳይንስ ትምህርቶችን በቤተ ሙከራ በተግባር ማገዛቸውን ተናግረዋል። ይህንንም በቀጣይ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት።

ቅዳሜ እና እሁድ ሲሰጡት የነበረው የማጠናከሪያ ትምህርትም ለውጤቱ መገኘት ምክንያት ነበር ብለዋል።

በ2016 ዓ.ም ተፈታኞች ላይ የነበረው ክፍተት በርትተው እንዲሠሩ እንዳደረጋቸው ያስታወሱት ደግሞ የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አብራራው ሞገስ ናቸው። ተማሪዎችን የሚመዝኑበት መንገድም ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

ለተማሪዎች በትምህርት ቤቱ የአዳር ጥናት ፕሮግራም በማዘጋጀት እርስ በርስ እንዲተጋገዙ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱንም ገልጸዋል። ለተማሪዎች ትልቁ ውጤት ከወላጆች ጋር ያለው ግንኙነት መልካም መኾን እንደኾነም ርእሰ መምህሩ ተናግረዋል። ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እየበሩ አዕምሮ የትምህርት ቤቱን መልካም ተሞክሮ ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ለማስፋት እየተጠቀሙበት መኾኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በዳግማዊ ቴዎድሮስ ትምህርት ቤት ያለውን መልካም ጅምር አንስተዋል።

ውጤታማ ትውልድን ለማፍራት በሁሉም ትምህርት ቤቶች ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን ማስፋት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መኾኑን ነው አቶ እየበሩ የገለጹት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕል ፍርድ ቤቶችን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
Next articleበበጀት ዓመቱ ከ780 በላይ የውኃ ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል።