
ባሕር ዳር: መስከረም 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የዳኞች ጉባኤ እየተካሄደ ነው። “የጋራ ራዕይ ለጠንካራ የዳኝነት ሥርዓት” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ የሚገኘው ጉባኤ በዛሬ ውሎው በባሕል ፍርድ ቤቶች ላይ ይመክራል።
በጉባኤው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የዛሬው ቀን “የባሕል ፍርድ ቤቶች ቀን” ተብሎ ተሰይሞ ውይይት እና ምክክር እንደሚደረግበት ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛውን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በመለወጥ ጥራት ያለው ፈጣን እና ተገማች የዳኝነት አገልግሎት እውን ለማድረግ ሰፋፊ የለውጥ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
በለውጥ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ውጤቶች እየተገኙ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
ከመደበኛው የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓት ጎን ለጎን አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ አንዱ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቅድሚያ የሚሰጠው እና ትልቁ ፕሮጀክት ኾኖ እየተሠራበት እንደሚገኝም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን የሚፈታበት ለዘመናት የቆየ እና የዳበረ ቱባ ባሕል ባለቤት ነው ብለዋል።
ይህንንም መሠረት በማድረግ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2017 ዓ.ም በጥናት ላይ ተመሥርቶ የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ለክልሉ ምክር ቤት አቅርቦ የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና ዕውቅና ለመስጠት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 298/2017 ዓ.ም አጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረጉን አንስተዋል።
የዚህ አዋጅ መውጣት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን የማይቃረኑ ባሕሎች እንዲያድጉ እና እንዲጎለብቱ ያደርጋል ነው ያሉት። ፍርድ ቤቱ ባሕሎች እንዲያድጉ እና እንዲጎለብቱ ሕገ መንግሥታዊ ኀላፊነት ያለበት መኾኑን ነው የተናገሩት። ክልሉ በግጭት አፈታት በኩል ያለውን ባሕሉን ለማሳደግ እንደሚያስችለውም ተናግረዋል።
ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች እውነትን በቀላሉ በማውጣት እና አለመግባባቶችን እርቅን መሠረት አድርጎ በመፍታት የሚሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል። ይህም በማኅበረሰቡ መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የባሕል ዳኝነት አሰጣጥ ሂደት ቀላል ቋንቋን እና ቀላል ሥነ ሥርዓትን የሚከተል እና ወጭ ቆጣቢ በኾነ መልኩ የሚካሄድ በመኾኑ ፍትሕን በቃላሉ ተደራሽ ያደርጋል ነው ያሉት።
በ2018 በጀት ዓመት የባሕል ፍርድ ቤቶችን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነውም ብለዋል። አጀንዳው በጠቅላይ ፍርድ ብቻ ሳይኾን በክልሉ መንግሥትም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራበት መኾኑን አስታውቀዋል።
አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የትግበራ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ አዋጁን መሠረት አድርጎ ዕውቅና ሊሰጣቸው የሚችሉ እና በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሥራ ላይ ያሉ የባሕል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ዓይነቶችን በጥናት የመለየት ሥራ አንደኛው ነው ብለዋል። የጥናት ሥራው መጠናቀቁንም አመላክተዋል።
የዛሬው መድረክ ዋና ዓላማም በአዋጁ ላይ ግንዛቤ መፍጠር እና አዋጁን ተከትሎ በተሠራው ክልል አቀፍ የትግበራ ጥናት ላይ ተወያይቶ በማዳበር ፍርድ ቤቱ በያዘው ዕቅድ እና ክልሉ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በ2018 በጀት ዓመት የባሕል ፍርድ ቤቶችን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሥራ እንዲጀምሩ ለማስቻል ነው ብለዋል።
በአዋጁ መሠረት የባሕል ፍርድ ቤቶች ተጠሪነት ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶች ከፍተኛ ኀላፊነት ተጥሎባቸዋል ነው ያሉት። የአካባቢ መሥተዳድሮች በተለይም የቀበሌ መዋቅሮች ይህንን አዋጅ በማስተግበር ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
የአዋጁን አፈጻጸም የሚከታተል፤ ለክልሉ ምክር ቤት ተጠሪ የኾነ እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰብሳቢነት የሚመራ የባሕል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት መቋቋሙንም አስታውቀዋል።
የክልሉ ፍትሕ ቢሮ፣ የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የሴቶች፣ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ፣ የፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት እና የክልሉ ጠበቆች ማኅበር የምክር ቤቱ አባላት መኾናቸውንም አንስተዋል።
ሁሉም በባሕል ፍርድ ቤት ዳኝነት አሰጣጥ የሚሳተፉ ሽማግሌዎች የሚወከሉበት እና በክልል ደረጃ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ በየአካባቢው ደግሞ በዓመት አንድ ጊዜ እየተገናኙ በባሕል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አሰጣጥ ላይ የሚመክር የሽማግሌዎች ጉባኤ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል ነው ያሉት።
በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶች፣ የቀበሌ መሥተዳድሮች፣ በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አሥፈጻሚ አካላት፣ ሌሎች የፍትሕ ተቋማት፣ የአማካሪ ምክር ቤቱ አባል ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና መላው የክልሉ ሕዝብ ለዚህ አዋጅ መፈጸም እና ለክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች መዳበር የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ሕጉን በማርቀቅ፣ የትገበራ ፍኖተ ካርታውን እና ጥናቱን በመሥራት ለተሳተፉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!