
ባሕር ዳር: መስከረም 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወቃል። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደግሞ የትምህርት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ከቆየባቸው አካባቢዎች ውስጥ አንዱ ነው።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የተማሪ ወላጅ እንደገለጹት በአካባቢያቸው ትምህርት ተዘግቶ መቆየቱን ነግረውናል። በዚህም ተማሪዎች ተስፋ እየቆረጡ ወደ ስደት የሄዱ እና ሴት ልጆች ያለ ዕድሜያቸው ወደ ትዳር የገቡ መቆየታቸውን ለአሚኮ ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት ማኅበረሰቡ ተወያይቶ ትምህርት መጀመሩን ነው የተናገሩት። በዚህም በአካባቢያቸው ያሉ ተማሪዎች እና ወላጆች ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በዚሁ ወረዳ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ እያስተማሩ ያሉ መምህር እንደገለጹልን ትምህርት በመቋረጡ ተማሪዎች፣ መምህራን እና ወላጆች ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በ2018 የትምህርት ዘመን ትምህርት ለማስጀመር መምህራን ከማኅበረሰቡ እና የተማሪ ወላጆች ጋር በመወያየት መግባባት ላይ ደርሰዋል ነው ያሉት፡፡ በዚህም ተማሪዎች፣ መምህራን እና ወላጆች መደሰታቸውን አንስተዋል፡፡ ምዝባው ቀደም ብሎ ተጠናቅቆ የመማር ማስተማር ሥራው ተጀምሯል ብለዋል፡፡
ሌላው በወረዳው የአንድ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር እንደተናገሩት ትምህርት በተቋረጠበት ጊዜ በተማሪዎች እና መምህራን ላይ ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን አንስተውልናል፡፡
በያዝነው የትምህርት ዘመንም ትምህርት ለማስጀመር ከማኅበረሰቡ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን በመጠቀም አወያይተው ምዝገባው መሳካቱን ተናግረዋል፡፡ እንደ ትምህርት ቤት የያዙትን የተማሪዎች ምዝገባ ዕቅድ ማሳካታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ይህንን ለማሳካት ለማኅበረሰቡ ትውልድን ለማስቀጠል የተማረ የሰው ኀይል አስፈላጊ መኾኑን በማስረዳት ትምህርት እንዲጀመር ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ተማሪዎችም መምህራንም በቁጭት ወደ መማር ማስተማር ሥራው ሙሉ በሙሉ መግባታቸውን ነው የገለጹት፡፡
የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተመልከት አዲሱ ትምህርት ለማስጀመር ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በመጠቀም ከማኅበረሰቡ ጋር በመወያየት ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
ለምዝገባ ቅድመ ዝግጅት መረጃ በሌለባቸው ትምህርት ቤቶች የተማሪ ልየታ ሢሠራ ቆይቷል ነው ያሉት። የአንድ ጀምበር የሙከራ ምዝገባ ተካሂዶ በሦስት ትምህርት ቤቶች በአንድ ቀን መቶ በመቶ መዝግበዋል ነው ያሉት።
በወረዳው ካሉት 55 ትምህርት ቤቶች 47ቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከማስተማር ውጭ ነበሩ ብለዋል። አሁን ላይ 54ቱ ትምህርት ቤቶች ማስተማር መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ትምህርት በተጀመረበት አግባብ እንዲቀጥል ማኅበረሰቡን ባለቤት እንዲኾን እየሠራን ነው ብለዋል። ትምህርት ማኅበራዊ ተቋም በመኾኑ ማኅበረሰቡ በኀላፊነት ወስዶ እንዲሠራ እየተደረገ እንደኾነ ነው የገለጹት።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ክንዱ ዘውዱ ትምህርት በሚገባ መጀመሩን አንስተዋል። አሁንም ግን ገና ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።
ምዝገባ በተካሄደባቸው ትምህርት ቤቶች መምህራን ፈጥነው ወደ ሥራ ገብተዋል ነው ያሉት፡፡ ኾኖም አልፎ አልፎ ከማኅበረሰቡም ልጆቻቸውን ያላስመዘገቡ እንዳሉ ነው የተናገሩት፡፡
የምዝገባ መዘግየት የትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ያሉት ኀላፊው ተማሪዎችን በወቅቱ በማስመዝገብ ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩም አሳስበዋል፡፡
ተዘግተው የቆዩ የትምህርት ተቋማት ጉዳት የደረሰባቸው ስላሉ ጎን ለጎን ለመጠገንም ማኅበረሰቡ እና የሚመለከተው አካል ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!