
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ውሻን የሚያሳብድ በሽታ “ራቢስ” በሚባል ቫይረስ በተለከፉ እንደ ውሻ፣ ቀበሮ፣ ተኩላ እና ሌሎች እንስሳት ንክሻ አማካኝነት የሚመጣ እና ወደ ጤናማ ሰው ሊተላለፍ የሚችል አደገኛ በሽታ ነው፡፡
በሽታው በሌሊት ወፍ አማካኝነትም ሊተላለፍ እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ። ቫይረሱ ከእንስሳት ወደ ሰው እና ከእንስሳት ወደ እንስሳት የሚተላለፍ በሽታ ነው።
ከአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በሽታው በክልሉ ዋነኛ የኅብረተሰብ ጤና ችግር እየኾነ ይገኛል።
በሽታው የማኅበረሰብ ሥጋት እየኾነ መምጣቱን የነገሩን ከቋራ ወረዳ ወደ ባሕር ዳር ለሕክምና እንደመጡ የነገሩን ሰፊው መኮንን ናቸው።
አቶ ሰፊው እንዳሉት ታዳጊ ልጃቸው እንስሳት በማገድ ላይ እንዳለ በጎረቤት ውሻ ይነከሳል። በሕክምና ባለሙያ ምክረ ሃሳብ በአካባቢው በሚገኝ ጤና ጣቢያ ላይ ጊዜያ እርዳታ ከተደረገለት በኋላ ለተሻለ ሕክምና ወደ ባሕር ዳር እንደመጡም ነው የገለጹልን። አሁን ላይ ለአንድ ወር የሚወሰድ መድኃኒት ተሰጥቶት እየወሰደ ይገኛል ብለዋል።
አቶ ሰፊው የራሳቸውን ውሻ እንዳስከተቡ እና በግቢያቸው እየተንከባከቡ ቢኾኑም በርካታ ባለቤት የሌላቸው ውሾች የማኅበረብ ሥጋት መኾናቸውን ነው የገለጹልን። ባለቤት ያላቸው ውሾች እንዲከተቡ እና በግቢያቸው ታስረው እንክብካቤ እንዲደረግላቸው፤ ባለቤት የሌላቸው ውሾች ደግሞ እንዲወገዱ የሚመለከተው አካል ኀላፊነት ወስዶ እንዲሠራም ጠይቀዋል።
የእንስሳት ሕክምና ባለሙያ የኾኑት ነጻነት ስጦታው በግላቸው ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ውሻን እየከተቡ እንደሚገኙ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። ክትባቱን የሚሠጡት ደግሞ በግል ተቋማቸው እና ቤት ለቤት እንደኾነ ተናግረዋል።
በዚህም በመንግሥትም ኾነ በግል ተቋማት ማስከተብ የማይችሉ ዜጎችን ጉልበት፣ ጊዜ እና እንግልት መቅረፍ ተችሏል ብለዋል። በዚህ ዓመትም በርካታ ውሾችን መከተብ መቻሉን ነው የተናገሩት። ማስከተብ ለሚፈልጉ ሁሉ ካሉበት ድረስ ተገኝተው እንደሚከትቡ ነው ባለሙያዋ የገለጹልን።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የአደጋ ሥጋት ተግባቦት ቡድን መሪ ሀብታሙ አለባቸው በሽታው በክልሉ ዋነኛ የኅብረተሰብ ጤና ችግር እየኾነ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ሀገር ውሻን በሚያሳብድ በሽታ በተለይም ደግሞ ውሻን በሚያሳብድ በሽታ የተጠቃን ሰው ሪፖርት ከሚያደርጉ አካባቢዎች የአማራ ክልል ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል። የችግሩ ስፋት ቢለያይም ሥርጭቱ የክልሉን ሁሉም አካባቢዎች ያዳረሰ መኾኑንም ነው የተናገሩት።
በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ከ8 ሺህ በላይ በሚያሳብድ የውሻ በሽታ የተጠረጠሩ ሰዎች ሪፖርት መደረጉን እና ከ100 በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይዎታቸው ማለፉን በማሳያነት አንስተዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ደግሞ በየሳምንቱ በአማካይ እስከ 225 የሚደርሱ በሚያሳብድ የውሻ በሽታ የተጠረጠሩ ሰዎች ሪፖርት ይደረጋል ነው ያሉት።
አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ባሕላዊ ሕክምና ስለሚሄድ እና መረጃውን ስለማያገኝ እንጅ ወደ ዘመናዊ ሕክምና ቢመጣ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል።
በማኅበረሰቡ የሚታየው የውሻ አያያዝ እና የማስከተብ ልምድ ማነስ ውሻን ለሚያሳብድ በሽታ መጨመር ምክንያት ኾኗል ነው ያሉት። እንደ ክልል ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ውሾችን ማስወገድ አለመቻል እና ለሰዎች የሚሰጠው የደኅረ ተላጭነት ክትባት እጥረት ለችግሩ መስፋት ሌላኛው ምክንያት ኾኗል ብለዋል። “ችግሩ አሳሳቢ የማኅበረሰብ ችግር እየኾነ እንደመጣም” ገልጸዋል።
በሽታውን ለመከላከል ማኅበረሰቡ ውሾችን ማስከተብ፣ አስሮ መንከባከብ፣ ችግሩ ከተከሰተ ወዲያውኑ በውኃ እና በሳሙና መታጠብ ቀዳሚው መፍትሔ መኾኑንም ገልጸዋል።
ከታጠቡ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሕክምና ተቋማት በመሄድ የድኅረ ተጋላጭነት ክትባት ማግኘት ከቻሉ ሞትን መቀነስ ይቻላል ነው ያሉት።
ባለቤት አልባ ውሾችን ለማስወገድ እና ጉዳት ያደረሰውን ውሻ ባለቤት ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችል ሕግ ተዘጋጅቶ ለክልል ምክር ቤት መቅረቡንም ቡድን መሪው ጠቁመዋል። ሕጉ ከጸደቀ ችግሩን መቅረፍ ይቻላልም ነው ያሉት። የሚመለከታቸው ተቋማትም የበሽታውን አሳሳቢነት በመረዳት በተቀናጀ መንገድ እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!