
ደብረ ብርሃን: መስከረም 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን እና ደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የትምህርት ተቋማት የ2018 ትምህርት አጀማመር ግምገማ ተደርጓል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ ትምህርት ከገጠመው ወቅታዊ ችግር አኳያ ውጤት ለማስመዝገብ ሰፊ ርብርብ የሚጠይቅ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡
በከተማው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት በትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ከተማ አሥተዳደሩ የሚቻለውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራው በሁሉም ተቋማት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
የተማሪዎች ምዝገባም ይሁን የተመዘገቡ ተማሪዎችን በማስተማር በኩል ያለው አፈጻጸም የተሻለ ነው ብለዋል፡፡
የትምህርት ሥራን ውጤታማ ለማድረግ ለትምህርት ምቹ ከባቢን ለመፍጠር ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ግን አፈጻጸሙ ውስንነት እንዳለው ጠቅሰው በቀጣይ ሽፋኑን በማሳደግ በተለየ ተልዕኮ ችግሩን መቅረፍ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኅላፊ ጸጋዬ እንግዳወርቅ በዞኑ ካሉ ትምህርት ቤቶች 2 ሺህ 13 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተማሪ ምዝገባ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ የሁለተኛ ደረጃ የተማሪዎች የምዝገባም ይሁን በትምህርት ተቋማቱ ተገኝተው ትምህርታቸውን የመከታተል ምጣኔ ዝቅተኛ መኾኑን እሳቸውም ተናግረዋል፡፡
ከተማሪዎች እና ወላጆች ጋር የጋራ መግባባት በመፍጠር አሁንም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ መሠራት እንደሚገባ ያነሱት መምሪያ ኀላፊው ለዚህም የአጋር አካላት ርብርብ በእጅጉ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ አማካሪ ካሳሁን አዳነ ትምህርት የአንድ ሀገር መፃኢ እድልን የሚወስን በመኾኑ ለሽፋኑም ይሁን ጥራት ያለው የመማር ማስተማር ከባቢ ለመፍጠር ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ኀላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
እስከ መስከረም 30 /2018 ዓ.ም ድረስ በሁሉም የትምህርት እርከኖች ወደ ትምህርት ተቋማት ያልገቡ ተማሪዎችን በመለየት እንዲመለሱ ለማድረግ የትምህርት ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ:- ገንዘብ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን