“በአንድ ሳምንት ብቻ 30 ሺህ የሚጠጉ የወባ ሕሙማን ተመዝግበዋል” የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

5
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የአርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ” በሚል የሚደረገው ወባን የመከላከል ክልል አቀፍ ዘመቻ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተጀምሯል።
በአማራ ክልል በአንድ ሳምንት ብቻ 30 ሺህ የሚጠጋ የወባ ሕሙማን መመዝገቡን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ አስታውቋል።
በቀጣይም የሙቀት መጠኑ እየጨመረ ስለሚሄድ የወባ ስርጭትም እንደሚጨምር ነው ኢንስቲትዩቱ የገለጸው።
የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምስክር ሰውነት ወጣቶች በየአካባቢው ውኃ የሚያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስ ወባን በመከላከሉ ረገድ ዋነኛ ተዋናይ መኾን ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የወጣቶች ክንፍ ኀላፊ ተስፋሁን ተሰማ ወጣቶች ባላቸው ጊዜ ማኅበረሰቡን በበጎ ፍቃድ እያገለገሉ እንደሚገኙ አስታውሷል።
የወባ በሽታ ከመከሰቱ በፊት ወጣቶች በየአደረጃጀታቸው በዘመቻ መልክ የበሽታው የመከሰቻ ቦታን የማጽዳት ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉም ብሏል። በዚህም ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ሥራ ወጣቶች ዋነኛ አጋዥ በመኾናቸው ይጠበቅባቸዋል ነው ያለው።
ወጣቶች በክረምት ያሳዩትን የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በበጋም ወባ ላይ በመዝመት ማስቀጠል መቻላቸውን ነው ወጣት ተስፋሁን የተናገረው።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በ2017 ዓ.ም 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በበሸታው መጠቃታቸውን አስታውሰዋል። በኅብረተሰቡ፣ በአጋር አካላት እና በመንግሥት ርብርብ ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርስ አክሞ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።
የወባ በሽታ አሁንም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በከፍተኛ ኹኔታ እየተከሰተ መኾኑን ነው አቶ በላይ የተናገሩት።
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም በዚህ ሳምንት ብቻ በክልሉ 30 ሺህ የሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በወባ ተጠቅተዋል ነው ያሉት።
አንድም ሰው በወባ በሽታ መሞት የለበትም ያሉት አቶ በላይ በሽታውን ለመከላከል ሁሉም መረባረብ ይኖርበታል ብለዋል።
“በእጅ እፍኝ” ውኃ በርካታ የወባ ትንኝ መራባት እንደሚችልም ተናግረዋል። ስለዚህም በማንኛውም ቁስ ያቆረ ውኃ መፋሰስ አለበት ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ ከ4 ሚሊዮን በላይ አጎበር ያስፈልጋል ያሉት አቶ በላይ እስካሁን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአልጋ አጎበር ተገኝቷል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የወልድያ ከተማን የኮሪደር ልማት ጎበኙ።
Next articleየክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የደም ልገሳ አደረጉ።