
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 06/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአፍሪካ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ስርጭት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና መቼ እንደሚጀምር ለመግለፅ አዳጋች ቢያደርገውም ምሥረታውን በበላይነት እንዲከታተል ኃላፊነት የተሰጠው አካል ትናንት በሰጠው መግለጫ በመጪው ዓመት (እ.አ.አ) ጥር 1/2021 ሊጀምር ይችላል ብሏል፡፡
የሥራ አስፈፃሚ ቦርዱ ባካሄደው በቴክኖሎጂ የታገዘ ውይይት ላይ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ዋና ጸሐፊ ዋማሌ ማኔ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚጀመርበት ጊዜ በቫይረሱ የስርጭት ሁኔታ እንደሚወሰን ተናግረዋል፡፡
“ነፃ የንግድ ቀጣናው በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሥራ እንዲጀምር ምክረ ሐሳብ አቅርበናል፤ ነገር ግን በወረርሽኙ የስርጭት ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል” ነው ያሉት ዋና ፀሐፊው፡፡
የንግድ ስምምነቱ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ወደ ሥራ መግባት ነበረበት፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ክትባት እስኪገኝለት ድረስ ስርጭቱ ሊቀጥል እንደሚችልም አስጠንቅቋል፡፡ በዋናነት ዋማሌ ማኔ በርካታ ሀገራት በወረርሽኙ ምክንያ ድንበሮቻቸውን ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ዝግ ማድረጋቸው ነፃ የንግድ ቀጣናውን ለማስጀመር ውስብስብ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የዓለም ንግድ ድርጅት በ1994 (እ.አ.አ) ከተመሠረተ በኋላ በምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳው ታላቁ ይሆናል ተብሏል፡፡ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ሕዝቦችን ከ3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በሆነ የንግድ ትስስር ያጎዳኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አባል ሀገራቱ በመጪዎቹ ስድስት ወራት የንግድ ቀረጥ ድርድሩን እንደሚጨርሱ እምነት እንዳላቸውም ማኔ ጠቁመዋል፡፡
ምንጭ፡- ሲጂቲኤን
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡