ልጆች እንዳይማሩ ማድረግ የትውልድን ነገ ማጨለም ነው።

6
አዲስ አበባ: መስከረም 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ የተፈጠረውን
የትምህርት ችግር ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚዲያ አካላት ጋር ተወያይቷል።
የዓለም ኃያላን ሁሉ መሠረታቸው ትምህርት እና የተማረ የሰው ኃይል ነው። በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዳይመጡ እንቅፋት ኾኗ ቆይቷል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ሕጻናትን ወደ ትምህር ቤት አለመላክ እና እንዲማሩ አለመፍቀድ የትውልድን የነገ እጣ ፈንታ በፈተና የተሞላ የማድረግ ተግባር መኾኑን ገልጸዋል። “ልጆች እንዳይማሩ ማድረግ የትውልድን ነገ ማጨለም” ነው ብለዋል። ሁሉም ማኅበረሰብ ለችግሩ መፍትሔ መሻት አለበት ነው ያሉት።
ይሄን በማድረግ የልጆችን የመማር መብት ልናስጠብቅ ይገባል ብለዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፉ ከሠለጠኑ ሀገራት ጋር አብራ የጀመረች እና ለዘርፉ የላቀ እሴት ያላት ሀገር መኾኗን ገልጸዋል። አሁን ላይ ወደፊት መራመድ ሲገባ ትውልድን ከትምህርት ገበታው ነጥሎ ወደ ኋላ የመመለስ አዝማሚያ እየታየ ነው ብለዋል።
ሚዲያዎች የትምህርትን ቁልፍ መሳሪያነት የሚያሳዩ፣ በዘርፉ የገጠመውን ጉዳት እና መውጫ መንገድ የሚያመላክቱ ሥራዎችን እንዲሠሩ ጠይቀዋል። ለልጆች የነገ ብሩህ ተስፋ እውን መኾን በሰፊው መሥራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ከዚህ በፊት በገጠመው የትምህርት ስብራት ዙሪያ ሽፋን ለመስጠት ሙከራዎች እንደነበሩ ገልጸዋል። በቀጣይ ጉዳዩን በትኩረት ለመዳሰስ ጥረት እንደሚያደርጉም አመላክተዋል።
የሀገር እና የትውልድ ግንባታ መሠረት ለኾነው ትምህርት ሁሉም ባለድርሻ አካል እንዲረባረብ እና የመፍትሔ ሀሳቦችን እንዲያመላክትም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጉልበት ሠራተኞችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታወቀ።
Next articleከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የወልድያ ከተማን የኮሪደር ልማት ጎበኙ።