
ባሕር ዳር፡ መስከረም ፡ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሰብል አሠባሠብ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ለሰብል ሥብሠባ የሰው ጉልበት እና ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል።
ለሰብል ሥብሠባ በርካታ የሰው ኃይል ከሚፈለግባቸው አካባቢዎች ደግሞ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አንደኛው ነው።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ነዋሪው አርሶ አደር እስክንድር ሳለው በ344 ሄክታር መሬት ጥጥ፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር እና ማሾ ማምረታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ 234 ሄክታር መሬቱ በሰሊጥ ምርት የተሸፈነ ነው፡፡
ምርቱ አሁን የመሠብሠቢያው ወቅት በመኾኑ ወቅቱን ጠብቆ ለመሠብሠብ እስከ 300 የሚደርሱ የጉልበት ሠራተኞች እንደሚያስፈልጓቸው ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የተሟላ መጠለያ፣ ምግብ፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን እንዳሟሉም ገልጸዋል።
አሚኮ ያናገራቸው ሌላው አርሶ አደር ጌታቸው ሽፈራው በ250 ሄክታር መሬት ላይ ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ አኩሪ አተር እና ማሾ እያመረቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የምርቱ ቁመና ሲታይ ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ መኾኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ የሰሊጥ፣ ማሾ እና አኩሪ አተር የማጨጃ ጊዜ በመኾኑ የሰው ኀይል እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከዚህ በፊት እንደሚያደርጉት ሁሉ ሠራተኞችን ለመቀበል የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው ያስገነዘቡት፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ ኑርሁሴን አብድልቃድር በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከ561ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
ከዚህ ውስጥ 310 ሺህ ሄክታር መሬት የሚኾነው በሰሊጥ፣ በማሾ እና አኩሪ አተር ምርት የተሸፈነ መኾኑን ተናግረዋል።
የሰሊጥ ምርት የመሠብሠቢያ ወቅቱ በመድረሱ የዞኑ ግብርና መምሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካት ጋር በመኾን የምርት ብክነትን ለመቀነስ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም በቂ የሰው ኀይል ወደ ዞኑ እንዲመጣ እና እራሱን፣ አካባቢውን እና ሀገሩን እንዲጠቅም ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በዚህ ሥራ ላይ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኀይል ወደ አካባቢው ሲመጣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶችን በመለየት የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
አካባቢው ሰላም መኾኑን የተናገሩት ቡድን መሪው ለአማራ ክልል እና በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ የጉልበት ሠራተኞች ወደ አካባቢው መጥተው የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በዞኑ በቂ የኾነ የተደራጀ መጠለያ መኖሩን አስታውቀዋል። የጤና፣ የምግብ እና የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ጨምሮ የሚያስፈልገውን ግብዓት በበቂ ሁኔታ መቅረቡንም አብራርተዋል፡፡
የሰብል አጨዳ ሥራው አልፎ አልፎ መጀመሩን ያነሱት ቡድን መሪው በዋናነት ከመስከረም 27/2018 ዓ.ም ጀምሮ በስፋት እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
በዞኑ በዘር ከተሸፈነው ጠቅላላ መሬት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!