በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎች ላይ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች፦

5
ባሕር ዳር፡ መስከረም 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎች ሀሳባቸውን የሚለዋወጡበት እና መረጃ በቀላሉ ተደራሽ የሚኾንበት የመገናኛ አማራጭ ነው።
ይህ የመገናኛ አማራጭ በርካታ ጥቅሞችን የሚሰጥ ቢኾንም ያልተገደበ አጠቃቀም ይስተዋልበታል። ያልተረጋገጠ መረጃ የሚሰራጭበት እንደኾነም ይነሳል።
ከዚህ አንጻር የማኅበራዊ ሚዲያ የላቀ ጥቅም ቢኖረውም በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።
ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በርካታ የተሳሳቱ መረጃዎች ሲሰራጩ ይስተዋላል። የተዛቡ መረጃዎች በመሠራጨታቸውም አደገኛ ውጤቶችን እያስከተለ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ መረጃዎችን ተጠቅሞ የመረጃ ምንጭ አለመጥቀስ እና ለመጀመሪያ ደረጃ ምንጭ ዕውቅና ወይም ዋጋ አለመስጠት ከሚዲያም ኾነ ከጋዜጠኝነት መርሕ ያፈነገጠ ድርጊትም ነው።
በኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህርት ሕይወት ዮሐንስ ሀሰተኛ መረጃዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት እየተቀናበሩ ሚሰራጩበት አጋጣሚ እየታየ ነው ብለዋል።
ከሩቅ በመኾን የግለሰቦችን ፍላጎት ብቻ ለማስረጽ ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት መኖራቸውንም አመላክተዋል። የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የጋዜጠኝነት ሙያንም ጥያቄ ውስጥ የሚከት እየኾነ መምጣቱንም አንስተዋል።
ጉዳዩ ማኀበረሰቡን ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ለሥነ ልቦና ቀውሶች እንደሚዳርግ መምህር ሕይወት ተናግረዋል።
ተቋማትም ሆነ ግለሰቦች የመረጃ ምንጭ ሳይጠቅሱ መረጃ ማሰራጨት ተገቢው የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ክህሎት ካለመኖር የመነጨ እንደኾነ ገልጸዋል።
ተቋማት ለሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች መረጃ የማጣራት፣ የማደራጀት እና ማጋራት በተመለከተ በቂ ግንዛቤ መፍጠር ብሎም መተግበር እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
የመረጃ ምንጭ መጥቀስ መረጃው እንኳን ስህተት ኾኖ ቢገኝ ኀላፊነቱን የሚወስደው መጀመሪያ ያጋራው ሚዲያ በመኾኑ ከተጠያቂነትም እንደሚያድን ጠቁመዋል።
መረጃዎችን ከማሠራጨት እና ከማጋራት በፊት የመረጃውን ምንጭ ማጣራት፣ መረጃውን መተንተን፣ ማደራጀት እና ትክክለኛነቱን በማረጋገጥ መጠቀም እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።
ማኅበረሰቡም ዘመን ያመጣውን ቴክኖሎጅ ብቻ አምኖ ከመቀበል ይልቅ በአካባቢው ስላለው ኹኔታ በቅርበት ማጣራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል።
በመንግሥት በኩል ቁጥጥር ከሚደረግባቸው እና ተጠያቂ ከሚኾኑ የሚዲያ ተቋማት መረጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ መምህርት ሕይወት አስገንዝበዋል።
የእውነት ማጣራት ባለሙያ እና አሠልጣኝ አብነት ቢኾነኝ ማኅበራዊ ሚዲያ ለሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ምቹ አማራጭ እየኾነ መምጣቱን ተናግረዋል።
ሀሰተኛ መረጃ በሦስት ምክንያቶች እንደሚሰራጩ አቶ አብነት አስረድተዋል። መረጃን በማሳሳት (Mis information)፣ መረጃን በማዛባት(Dis information)፣ እና መረጃን በማደፍረስ ወይም በመበከል(Mal information) ሀሰተኛ መረጃ እንደሚሰራጭም ነው የጠቆሙት።
ማኅበረሰቡ ሐሰተኛ መረጃን በሁለት መልኩ ማጣራት እንደሚችል አንስተዋል። በመጀመሪያ መረጃውን ከተለያዩ ምንጮች በማየት ማረጋገጥ ይገባል።
በመረጃው ውስጥ የተጠቀሱትን የመረጃ አይነቶች፣ ተጓዳኝ የመረጃ አማራጮችን በማየት፣ ዝርዝሮችን እና ሕጋዊ ሰነዶች የተካተቱበት መኾኑን ማረጋገጥ አንዱ መንገድ መኾኑንም አንስተዋል።
በሁለተኛ ደረጃ የእውነታ ማጣሪያ ቴክኖሎጅዎችን እና መተግበሪያዎችን በመጠቀም ማጣራት እንደሚቻልም አስረድተዋል።
በተለይም በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተቀነባበሩ ፎቶዎችን እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ተጠቅመው የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በእውነታ ማጣሪያ መተግበሪያዎች መለየት እንደሚቻል ነው የተናገሩት።
ተቋማትም ለየራሳቸው የእውነታ ማጣሪያ አማራጮችን በመዘርጋት ትክክለኛ መረጃን ለማኀበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleዕውቅናው አደራ የተሰጠንበት ነው።
Next articleየጉልበት ሠራተኞችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታወቀ።