
ደሴ: መስከረም 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና መምህራን የዕውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል፡፡
መምሪያው የ12ኛ ክፍል ፈተናን ተፈትነው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ 94 ተማሪዎች፣ 53 መምህራን እና ለ4 የትምህርት የሥራ ኀላፊዎች ነው የማበረታቻ ሽልማት እና ዕውቅና የሰጠው፡፡
በዕለቱ ዕውቅና እና ሽልማት ከተሰጣቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ አና ብሩክ እና ተማሪ ሙሉቀን አለባቸው ላስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት ትልቁ ምስጢር ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀማቸው እንደኾነ ተናግረዋል።
የወላጆቻቸው እና የመምህራን ድጋፍም የጎላ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የተሰጣቸው ዕውቅና አደራም እንደኾነ ተናግረዋል። በቀጣይ የትምህረት ሕይወታቸው ላይ የበለጠ ውጤት በማስመዝገብ ለሀገር የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት መነሳሳት እንደፈጠረባቸውም ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍቅር አበበ ከተማ አሥተዳደሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትኩረት በመሥራቱ የተማሪዎች ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
ለውጤቱ መገኘት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻዎች ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። ተማሪዎች፣ መምህራን እና የትምህርት መሪዎች ኀላፊነታቸውን በትጋት በመወጣት አኩሪ ውጤት ማስመዝገባቸውን እንዲቀጥሉም አሳስበዋል፡፡
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የሀገር ፍቅር ስሜቱ የዳበረ ትውልድ እንዲፈጠር ትምህርት ላይ በልዩ ትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።
“የዛሬ ተሸላሚዎች የነገ ሀገር ተረካቢዎች በመኾናችሁ ውጤታማነታችሁን አጠናክራችሁ እንደምታስቀጥሉ በመተማመን ከተማ አሥተዳደሩ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል” ነው ያሉት።
በትምህርት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ብቻውን በቂ ባለመኾኑ ተማሪዎች የቀሰሙትን ዕውቀት እና ጥበብ ከምግባር ጋር አቀናጅተው ለሀገር በሚጠቅም ሥራ ላይ ሊያውሉት እንደሚገባም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ የትምህርት ሥራ ውጤታማ እንዲኾን የመሪዎች ሚና ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። የትምህርት የሥራ ኀላፊዎችን አቅም ለማሳደግ በክልል ደረጃ ተከታታይ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዝቅተኛ ውጤት በተመዘገበባቸው ትምህርት ቤቶች ያሉ መሪዎች ራሳቸውን በመገምገም ከችግሩ እንዲወጡም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- አንተነህ ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!