
ደባርቅ፡ መስከረም፡ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ አዲሱን የሲቪል ሰርቪስ የአሠራር ለውጥ መሠረት አድርጎ አገልግሎትን ማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እና ሁለንተናዊ ዕድገት ለማስመዝገብ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ማሻሻል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ላይ የሚነሱ ክፍተቶችን ለመሙላት በትብብር መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ኀላፊ ያሬድ አበበ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችሉ የክትትል እና ድጋፍ ሥራዎችን ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ለግንዛቤ ፈጠራ ሥራ የሚያግዙ የጋራ መድረኮችን መካሄዳቸውንም ነው ያስገነዘቡት።
ተቋማት የአሠራር ግልጸኝነት እና ተጠያቂነትን መሠረት ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ የአሠራር ሂደቶችን እንዲከተሉ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።
ዲጂታላይዝድ የአሠራር ሂደትን ለመዘርጋትም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ገንዘብ መምሪያ ኀላፊ የኛ ነጋ ዘመናዊ አሠራርን መዘርጋት ግልጸኝነት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚያገለግልም ነው የገለጹት።
አላስፈላጊ የሃብት ብክነትን ለመቀነስ እና በጀቶች ለታለመላቸው ተግባራት እንዲውሉ ለማድረግ ዘመናዊ አሠራር መዘርጋት እንደሚያግዝም ነው ያብራሩት።
በቀጣይም ተቋማት የማኅበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኀላፊ ይርዳው ሲሳይ ተቋማት አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ እንዲችሉ የዲጂታላይዜሽን ዘርፉን የተሻለ ማድረግ እንዳለባቸው ነው ያብራሩት።
ለውጥ የሚጀምረው ከአመለካከት እንደኾነ ጠቁመው የመንግሥት ሠራተኛውን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ ሰብዓዊ ልማት ላይ መሥራት ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት ዕውቅና የመስጠት መርሐግብርም ተካሂዷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!