የውኃ ጉድፍ በሽታ ምንድን ነው?

4
ባሕር ዳር፡ መስከረም ፡ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰው ልጅ በተለያየ ሕመም ሊጠቃ ይችላል። ብዙ ጊዜ ሰዎች ሕመም ሲሰማቸው ቶሎ ወደ ሕክምና ተቋም ከመሄድ ይልቅ በቤት ውስጥ ሕመማቸውን ማስታመም ይቀናቸዋል።ይህ ደግሞ ሕይወትን እስከማጣት የሚያደርስ ጉዳት ያመጣል።
በተለያዩ አካባቢዎች ዓለሞቸ፣ ለምለሞቸ፣ ደጋጎቸ እየተባለ የሚጠራ የበሽታ አይነት አለ። ብዙ ጊዜ ደግሞ የውኃ ጉድፍ በሽታ እየተባለ ይጠራል። ይህ አጠራር ሳይንሳዊ ውይስ ተለምዷዊ?
እንዲህ በተለያዩ ስያሜዎች የሚጠራው በሽታ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዴት ይታይ ይኾን ?
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት ወይዘሮ ብርቱካን ገደፋው ሕመሙ በምን ምክንያት እንደያዘኝ ባላውቅም እኔን ለሁለት ሳምንት፣ ልጄን ደግሞ ለሥድስት ቀናት አሞናል ይላሉ። ውኃ የቋጠረ እብጠት ሙሉ ሰውነታቸውን እንደ ወረራቸው እና በጣም እያሳከካቸው እንደነበርም ተናግረዋል።
ጥላ እንዳያገኝ በሚል በቤት ውስጥ በመጋረጃ በመደበቅ ፈንድሻ፣ አረቂ ፣ ቂጣ በማቅረብ ጨፌ በመነስነስ ጠዋት፤ ምሳ ሰዓት እና ምሽት በቀን ሦሥት ጊዜ ቡና በማፍላት በሽታውን እንደሚያስታምሙ ገልጸውልናል።
ቡናው ላይ የቀረበውን የቡና ቁርስ ምግብ ከኛ ውጭ ለሌላ ሳይሰጥ ሕመሙን እያስታመምን ቆይተናል ያሉት ወይዘሮ ብርቱካን የሰው ጥላ ካረፈባቸው እንደሚያገረሽ በማሰብም ከቤት ውስጥ እንደማይወጡ ነግረውናል።
ሕመሙም ከልጃቸው በበለጠ እሳቸው ላይ እንደበረታባቸው እና ልጃቸው ካሁን በፊት ክትባት ወስዶ ሰለነበረ ሕመሙ እንደቀነሰለት ገልጸዋል።
✍️ ይህ በሽታ በጤና ባለሙያዎች ምን ይባላል ?
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሕጻናት ትምህርት ክፍል መምህር እና የሕጻናት ሐኪም ዶክተር አላምረው አለባቸው “የውኃ ጉድፍ በሽታ” (Chickenpox) ወይም በሕክምናው ቋንቋ “ቫሪሴላ” (Varicella) በቫይረስ የሚመጣ የቆዳ ላይ በሽታ ነው ብለዋል።
ይህ በሽታ ተላላፊ እና በልጆች ላይ የተለመደ መኾኑን ገልጸዋል።
እንደ ዶክተር አላምረው አለባቸው ገለጻ የውኃ ጉድፍ በሽታ ዋና ዋና ምልክቶች የሚባሉት፦
👉 በሽታው ከመውጣቱ በፊት ትኩሳት፣ ራስ ምታት እና የድካም ስሜት ሊኖር ይችላል።
👉ሽፍታ ሌላው ምልክት ነው። ሽፍታው መጀመሪያ ላይ ቀይ ነጠብጣቦች ኾነው ይጀምራሉ፤ ከዚያም በውኃ የተሞሉ ትናንሽ አረፋዎች የመሰሉ ቁስለት ይፈጥራሉ።
👉 የዚህ ሕመም ሌላው ምልክት ማሳከክ ነው፤ ሽፍታው ከፍተኛ የኾነ የማቃጠል ወይም የማሳከክ ስሜት ሊኖረው ይችላል።
ይህ በሽታ ከአንድ ሰው ወደ ሌላው በቀላሉ ሊተላለፍ ስለሚችል አንዱ ልጅ (ሰው)ሲይዝ ሌላውም መያዙ የተለመደ ነው ብለዋል ዶክተር አላምረው።
ዶክተር አላምረው ሕመሙ ከተከሰተ በኋላ በቤት ውስጥ ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎችን ሲያስረዱ፦
👉 ለልጁ ዕድሜ እና ክብደት ተስማሚ የኾነ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት መስጠት ይገባል።
👉 ልጆች ሲያሳክኩ ሽፍታውን በመቧጨር ኢንፌክሽን ሊፈጠር ስለሚችል ጥፍሮቻቸውን መቁረጥ እና ማጽዳት አለባቸው።
👉 ልጆቹ ብዙ ፈሳሽ እንዲወስዱ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በአብዛኛው የውኃ ጉድፍ በሽታ በራሱ ጊዜ ከአንድ እስከ ሁለት ሳምንት ባለ ጊዜ ውስጥ ይድናል ያሉት ዶክተር አላምረው ነገር ግን ልጆች ክትባት ካልወሰዱ፣ ከዚህ በፊት ተይዘው የማያውቁ ከኾነ፣ በሽታ የመቋቋም አቅማቸው በተለያዩ ምክንያቶች የቀነሱ ከኾነ እና ምልክቶቹ እየባሱ ወደ ኢንፌክሽን ከሄደ ወይም ሌሎች የጤና ችግሮች ካሉባቸው የሕክምና ባለሙያ ማማከር አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል። ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንደሚመከርም ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡም ከአጉል ድርጊቶች በመቆጠብ በሽታው ሲታይ ወደ ዘመናዊ የሕክምና ተቋም በመምጣት ማግኝት ያለበትን ሕክምና በጊዜ ማግኝት ይገባዋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ተልዕኮን በአግባቡ መወጣት ይገባል።
Next articleየአፈር አሲዳማነትን በመከላከል ምርታማነትን ለመጨመር እየተሠራ ነው።