አካባቢን በማጽዳት ወባን በቀላሉ መከላከል ይቻላል።

4
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ከተማ በግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ ክልል አቀፍ የወባ ወረርሽኝ መከላከል ማስጀመሪያ ንቅናቄ እየተካሄደ ነው።
ንቅናቄው “የአርብ ጠንካራ እጆች የወባን ወረርሽኝን ይገታሉ” መርሐ ግብር አካል ነው።
በከተማዋ ከተለያዩ አደረጃጀቶች የተውጣጡ ወጣቶች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም በግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ በመገኘት ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ ናቸው የተባሉ ቦታዎችን እያጸዱ ነው።
በዘመቻው ላይ ከሚሳተፉት መካከል የፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ኑሪያ አሕመድ አንዷ ናት። በከተማዋ ያለውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመግታት የሚያስችል ሥራ በማከናወን የራሷን አስተዎጽዖ እያበረከተች መኾኗን ተናግራለች።
የወባ በሽታን እንዲከሰት ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ያቆረ ውኃ ነው ያለችው ኑሪያ ተፋሰሶችን በቀላሉ በማጽዳት እና ያቆረ ውኃን በማፋሰስ ስርጭቱን መግታት ይችላል ብላለች።
አንድ ሰው አካባቢውን በማጽዳቱ ከተማዋን ንጹሕ ያደርጋል፤ ጤናውንም ይጠብቃል ነው ያለችው። በመኾኑም ሁሉም ወጣት በየአካባቢው የወባ መራቢያ ቦታዎችን ቢያጸዳ ወባን በቀላሉ መከላከል ይቻላል ብላለች።
ከአማራ ክልል ወጣቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን የተወከለው ሙሉሰው ታዬ ባለፈው ዓመት በተከናወነው ተመሳሳይ መርሐ ግብር ላይም ተሳታፊ እንደ ነበር አስታውሷል።
በወቅቱም ውኃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስ፣ ቦዮችን በመክፈት እና ሳር በማጨድ ወባን ለመከላከል የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግሯል። ባለፈው ዓመት በተሠራው ሥራም ውጤት በመገኘቱ ዘንድሮም ተሳታፊ እንደኾነ ነው የተናገረው።
ወጣቶች በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ በመኾን ለወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የማዳረቅ ሥራዎችን ሊያከናውኑ ይገባልም ብሏል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ሲስተር ዓለም አሰፋ ወባን ከምንከላከልባቸው ዘዴዎች አንዱ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ነው ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ያለውን ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት በቀላሉ መከላከል የሚቻለውም የአካባቢ ንጽሕና በጋራ በመጠበቅ መኾኑን ተናግረዋል።
የክረምቱን መውጣት ተከትሎም እስከ ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ድረስ ወባ በከፍተኛ ሁኔታ ትራባለች ያሉት ኀላፊዋ ከሕክምናው በዘለለ ያቆረ ውኃን በማፋሰስ እና በማዳረቅ ወባን መከላከል አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ወባ በ2017 ዓ.ም በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በበሸታው መጠቃታቸውን አስታውሰዋል።
“የአርብ ጠንካራ እጆች የወባን ወረርሽኝን ይገታሉ” በሚል መርሐ ግብር በርብርብ የመከላከል ሥራ በመሠራቱ ወረርሽኙን መቀልበስ መቻሉን ተናግረዋል።
ዛሬ በባሕር ዳር የተጀመረው የንቅናቄ ሥራም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ይተገበራል ነው ያሉት።
ከመስከረም አጋማሽ እስከ ታኅሣሥ ወር ወባ በከፍተኛ ሁኔታ ስርጭቱ ይኖራል ያሉት አቶ በላይ ሁሉም ሰው አካባቢውን ለወባ ትንኝ መራቢያ የማያመች ማደረግ አለበት ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article” ኢሬቻ የኦሮሞ የምስጋና ስርዓት ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ተልዕኮን በአግባቡ መወጣት ይገባል።